የሳይንስ ኮሌጅ 8ኛው ትምህርታዊ ጉባኤ

ሳይንስ ኮሌጅ 8ኛውን አመታዊ አገር አቀፍ ትምህርታዊ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል

                                                    በሙሉጐጃም አንዱአለም

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ 8ኛውን አመታዊ ጉባኤ “Multidisciplinary Scientific Research for Improving the quality of life” በሚል መሪ ቃል በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና ለኮንፍረንሱ አዘጋጆች የምስጋና መልእክታቸውን አስተላልፈው የተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያላቸው ተቋማት አብረው የመስራት ልምድን እንዲያዳብሩ ጉባኤው በር ከፋች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በማስከተልም ሳይንስ በሳይንስነቱ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን ሊቀርፍ የሚችለው ከሌሎች ሙያተኞች ጋር በቅንጅት ሲሰራ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ በአንክሮ ጠቁመዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የአብክመ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኮሚኒኬሽን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሰብስበው አጥቃው እስካሁን የነበሩት የምርምር ስራዎች በፅንሰሃሳብ ደረጃ ላይ የሚያተኩሩ ስለሆኑ  ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ተግባር ለመለወጥ ቁርጠኝነት ማሳየት እንደሚገባቸውና የቅንጅት ስራው መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ የድህረ ምረቃ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ዲን ዶ/ር ፀጋየ ካሳ የኮንፍረንሱ ዋና አላማ የተለያዩ ሙሁራን በተለያዩ ጊዜያት የሰሩአቸውን የምርምር ውጤቶች ቀርበው አንዱ ከሌላው የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ታልሞ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በጉባኤው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ጥናትና ምርምር አቅራቢዎች፣ጥሪ የተደረገላቸው ባለሙያዎች፣ መምህራንና፣ ተማሪዎች ታድመውበታል፡፡