የሞሸ ኮንቬንሽን

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ላይ ተሳተፈ
--------------------------------------------------------------------------
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያውን የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ወደ “እውቀት መር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ሀሳብ ሐምሌ 05/2013 ዓ.ም. ያስጀመረ ሲሆን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በፕሬዚደንቱ፣ ምክትል ፕሬዝደንቶችና ሳይንቲፊክ ዳሬክተሮች እንዲሁም በሌሎች አመራሮችና የኤግዚቢሽን አስጎብኝዎች በመወከል ተሳታፊ ሆኗል፡፡
ኮንቬንሽኑ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ርዕሰ ብሔር ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን በኤግዚብሽን ጉብኝት መርሃ ግብር ላይም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ይዟቸው የቀረበባቸውን የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የፈጠራ ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ በዕለቱም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራዎች በተለያዩ ሚኒስትሮች፣የግል እና የመንግስት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለኤግዚቢሽን ካቀረባቸው ስራዎች መካከልም በአግሮ ሜካናዜሽን፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን፣ በጤና፣ በጨርቃጨርቅ እና ፋሽን ዲዛይን እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያከናወናቸው የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የፈጠራ እና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ይገኙበታል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ሌሎችም የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተለያዩ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የፈጠራ ስራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን የእርስበርስ ትስስር እና የልምድ ልውውጥ እየተካሄደበት ይገኛል፡፡
ኮንቬንሽኑ እስከ ሃምሌ 8/2013ዐ ዓ.ም ድረስ የፈጠራና የምርምር ስራዎችን የማበረታታት፣ እዉቅና የመስጠትና ትስስር የመፍጠር ዓላማውን እያሳካ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡