የህፃናት ሞግዚቶች ስልጠና

ለህፃናት ሞግዚቶች ስልጠና ተሰጠ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ስር ያለው የህፃናት ማቆያ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ የቆየ ሲሆን  ስራ ለመጀመር በቅድሚያ ለሞግዚቶች ለአምስት ተከታታይ ቀናት በዩኒቨርሲቲው የስልጠና ማዕከል ሙያዊ ስልጠና ተሰጠ

ስልጠናው በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ብርሃኔ መንግስቴ ስልጠናው ከዩኒቨርሲቲው የስልጠና ማዕከል  ጋር በመተባበር የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በማስከተል የስልጠናው ዋና ዓላማ ከአሁን በፊት የነበረው አሰራር ልምድ ያላቸው ሞግዚቶች ከውጭ ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበርና አሁን ግን በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የስራ ክፍሎች ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞች በደረጃ እድገት በመመደባቸው ለስራው አዲስ ስለሆኑ ስለህፃናት አያያዝና የመጀመሪያ እርዳት አሰጣጥ ስልጠና ለመስጠት ታልሞ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

ዳይሬክተሯ አክለውም ለስራው የተመደቡት ሰራተኞች ስልጠናውን በነቃ ተሳትፎ መከታተል እንደሚገባቸውና ትኩረት ሰጥተው ህፃናትን በአግባቡ መንከባከብ እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

ከአሰልጣኞች መካካል አንዱ አቶ የኔነህ አያሌው በዩኒቨርሲቲው ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህፃናት ጤና አጠባበቅ መምህር ሲሆኑ ለሰው ልጅ እድገት መሰረቱ ህፃናትን በአግባቡ መንከባከብ እንደሆነ ገልፀው ስልጠናው አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ቀጣይነት እንዲኖረው መክረዋል፡፡ በተጨማሪም ለህፃናት የሚሰጠው ትኩረት ለየት ማለትና ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በቀጣይነት ሞግዚቶች በስራው ላይ ሲሰማሩ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንዴት መፍታት እንደሚችሉ የሚገልፁበት መድረክ መፈጠር እንደሚገባና የሰራተኞች ስብጥርም የጤና ባለሙያ ቢካተትበት የሚል ምክረ ሃሳብ አቶ የኔነህ አያሌው ለግሰዋል፡፡

ሰልጣኞችም በበኩላቸው ከስልጠናው ያገኙት ክህሎት ጥሩ እንደሆነና ለወደፊት ከስራቸው በዘለለ ለራሳቸው ልጆች አመጋገብ፣ አያያዝ፣ንፅህና አጠባበቅ፣ባህሪአቸውን መረዳት እንዲሁም አጠቃላይ የህፃናት እንክብካቤ ምን እንደሚመስል ሰፊ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡