ዘመናዊው ትምህርታችን እና ኢትዮጵያዊ ባህላችን

 ዘመናዊው ትምህርታችን እና ኢትዮጵያዊ ባህላችን  

ዘመናዊ ትምህርታችን እና ኢትዮጵያዊ ባህላችን ምንና ምን? በሚል ርዕስ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች በተገኙበት በዋናው ግቢ መሰብሰቢያ አዳራሽ አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡

የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማእከል ዳይሬክተር ዶ/ር አስቴር ሙሉ የውይይት ሐሳብ ለማቅረብ የተገኙ እንግዶችን  አመስግነው ማዕከሉ የተለያዩ ባህላዊና ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችን በማቅረብ የዩኒቨርሲቲችንን ማሕበረሰብ እያዝናና በማስተማር፣ እንዲሁም ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደየ ድርሻው እንዲወጣ ለማሳሰብ ዕድሎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ‹‹አንድን ሀገር ለመግደል፣የጦር መሳሪያ ወይም ወታደር አያስፈልግም፣የትምህርት ስርዓቱን መግደል ነው›› እንዲሉ፤ምንም እንኳን ስለትምህርት ለሚደረግ ውይይት ይህ አዲስና የመጀመሪያ ባይሆን ምናልባት በዚህ ርዕስ ላይ ለመወያየት ዛሬ ምን ተገኘ የሚል ጥያቄ በአንዳንዶቻችን አእምሮ ሊመጣ ይችላል ያሉት ዶ/ር አስቴር የለውጥ ጭላንጭል ለማየት አሁንም አይረፍድም ብለዋል፡፡

ኃላፊዋ አክለውም ዛሬ ሀገራችን ያለችበት ምስቅልቅል ሁኔታ፡- በተለይም የችግሮቻችን መፍትሄ ሊሆኑ የሚገባቸው ‹‹ሙሁራኖቻችን›› መፍትሄ መሆኑ ቀርቶ የችግር ምንጪ ሲሆኑ እያየን  መምጣታችን፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአስር ዓመት ስልታዊ ዕቅድ ማቅረቡን ተከትሎ ዕቅዱ ላይ ለሚደረግ ውይይት ገንቢ ሃሳቦችን ማቀበል ተገቢ ነው ብለን በማመናችን፤ ጥሩ ነገርን ለመስራት እና ለመፍጠር የሚሉት ለዛሬው መወያያ ርዕስ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልፀውልናል ፡፡

በፓናል ውይይቱ ፕ/ር ሹመት ሲሻኝ፣ ፕ/ር አለማየሁ ቢሻው፣ ዶ/ር ታደሰ መለሰ እና አባ በአማን ግሩም በሀሳብ አፍላቂነት እንዲሁም ዶ/ር ማረው አለሙ በአወያይነት ተሳትፈውበታል፡፡

ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ዘመናዊ/አውሮፓዊው ትምህርትን ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፅኖ የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው ይህን ማስቀረት የሚቻል እንዳልነበረ ነገር ግን በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታዎች እንዲቃኝ አለመደረጉ ዋናው ችግር ሆኖ ዘልቋል ብለዋል፡፡ በዘመኑም ኢትዮጵያ ጥንካሬዋ የተዳከመበት መሆኑ በምክንያትነት መነሳት ይችላል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለውም  ሀገራችን ከ13-16 ክፍለ ዘመን በታሪክ፣ ባህል እና በመንፈሳዊነት ከፍተኛ እምርታ አሳይታ የነበረች መሆኑን አውስተው የስልጣን መተካካት አለመኖር ግን ወደ ማያቆም ቁልቁሎሽ እንድንሄድ እንዳደረገን ጠቁመዋል፡፡ ዘመናዊው ትምህርት ሲጀመር ሀገራዊ ሁኔታን ያላየ ለመሆኑ ፕሮፌሰሩ በተማሩበት ከአራት አስርዮሽ በፊት ስለ አድዋ የሚያነሳ ምንም አይነት የትምህርት ይዘት እንዳልነበረ አስታውሰዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሹመት በመጨረሻም አሁን ያለውን ተጨባጭ እውነታ ማጤን እንደሚገባ እና የሞቱ፣ ሳንጠቀምባቸው ያመለጡንን ባህላዊ እሴቶች መልሶ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ትርፉ መጋጋጥ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ፕ/ር አለማየሁ ቢሻው በበኩላቸው ዘመናዊው/የአስኳላው ትምህርት አጀማመርን አስመልክተው ታሪካዊ ኩነቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ከ19ኛው የመጨረሻ ሩብ ከጣሊያን ጦርነት ማግስት በአፄ ምኒሊክ የተጀመረ መሆኑን ጠቁመው ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙትና ግብፃዊ የሆኑት ሊቀ-ጳጳስም ተጠቃሽ እንደሆኑ አውስተዋል፡፡ ዋናው ችግርም ከራሳችን ጋር የተዋሀደ አለመሆኑን ተናግረው. ስለ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች አንድ አጥኚ የተናገሩት ሁኔታውን ይገልፀዋል ሲሉ እንዲህ አስታውሰዋል፡- “There is nothing Ethiopian except the children.”

ዶ/ር ታደሰ መለሰ በበኩላቸው ዘመናዊ እና ባህላዊ የሚለውን ክፍፍል እና የእኛው ባህላዊ መባሉ “አእምሯችን በቅኝ ግዛት” ውስጥ እንደሆኑ ጠቋሚ ነው ሲሉ የጥበብ ባለቤቶች መሆናችንን መቀማታችን ማሳያ አው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ትምህርት በአርአያነት ሊወሳ የሚገባው ነገር እንዳለ አንስተው ለአስኳላ ትምህርት ተማሪዎች ምሳሌ መሆን የሚችል ታታሪነት እርስ በእርስ የመሟገት እና የመማማር የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ሃሳብ አቅራቢ አባ በአማን ግሩም ኢትዮጵያዊ በሆኑ የሃይማኖት ተቋማት በዋናነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሚሰጠው የማስተማር ዘዴ ተማሪ ተኮርነትን፣ የግምገማ ስርአቱን ግልፀኝነት፣ ተማሪ ማብቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ የተማሪዎችን የተለያየ ትምህርት የመቀበል አቅም ያማከለ መሆኑ እና ሌሎች እንደጥንካሬ ተወስዶ ሊዳብር ይገባው እንደነበር ጠቁመው ከዚህ በተቃራኒው በፅሁፍ ትምህርትን የሚያስተላልፉ ሰዎችን እንኳን አሉታዊ ቅፅል ስሞች ይሰጡ እንደነበር በቁጭት አውስተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ለመፍጠር ሀገር በቀል የግብረ-ገብ ትምህርት እና ሌሎች አገራዊ እሴቶችን ያካተተ ስርዓተ ትምህርት እንዲኖር እንዲሁም ዘመናዊው ትምህርት እና ኢትዮጵያዊ ባህላችን መካከል የሚስተዋሉ ልዩነቶችን አጉልቶ ማውጣት እና መፍትሄ ማፈላለግ በተሳታፊዎች በዝርዝር ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ የሚባሉ ባህላዊ እሴቶችን የመለየት፣ የማያሥፈልጉትን ለይቶ የማሻሻል እና የመሳሰሉት ትልቅ ስራ የሚጠይቁ መሆናቸው ተነስቷል፡፡

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት አቶ ብርሀኑ ገድፍ ባህል ማእከሉን፣ የውይይቱ ሀሳብ አቅራቢ ምሁራንና ተሳታፊዎችን አመስግነው ምሁራን ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት አልፈው አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ትርጉም ያለው ስራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንደዚህ ላሉ ጠቀሜታቸው ጉልህ የሆኑ ምሁራዊ ውይይቶችን እንደሚደግፍ አረጋግጠው የተሳታፊውን ቁጥር ለማሳደግ ስራ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡