ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባዔ

ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባዔ ተካሄደ

********************************************

(ሀምሌ 23/2014 ዓ.ም፣ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-BDU) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ‹‹መረጃ ለማይበገር የጤና ስርዓት ›› በሚል መሪ-ቃል ከሀምሌ 22 እስከ 24/2004 ዓ.ም የሚቆይ ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ተካሄደ፡፡

ጉባዔውን ያስጀመሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል በመገንባት ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፕ/ር የሺጌታ ገላው ለጉባኤ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት ኮሌጁ ከቅድመ ምረቃ እስከ ፒ.ኤች.ዲ እንዲሁም ከሜዲካል ዶክተር እስከ ድህረ-ስፔሻሊቲ ድረስ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቃት ያላቸው ዓለም-አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል፡፡ በምርምር ዘርፍም ችግር ፈችና ዘርፈ ብዙ ምርምሮችን በማድረግ ተቋማዊ ሀላፊነቱንና ሃገራዊ ድርሻውን በመወጣት ላይ የሚገኝ ሩቅ የሚያልም ኮሌጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕ/ር የሺጌታ አክለውም ኮሌጁ በተለይም ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ዘመናዊና ወቅቱ ያፈራቸውን የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ለሀገራችን ሕዝቦች ጥራት ያለውና የላቀ የሕክምና አገልግሎቶት በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮዽያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ እንደተናገሩት በሁሉም ዘርፍ የሚደረጉ የጤና ምርምሮች ተሰርተው የሚቀመጡ ሳይሆን በጤና ፖሊሲው በሚቀመጡ ስትራቴጅዎች ተካተው ለማህበረሰብ ጤና ልማት እንዲውሉ መደረግ ስላለባቸው የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የምርምር ጉባዔ በማዘጋጀቱ የሚመሰገን ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

በዕለቱ የጥናት ፅሁፍ ያቀረቡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ታደሰ ኃይሉ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅም ሆነ የአብክመ ጤና ኢንስቲትዩት ጤናማ ማህበረሰብን መገንባት ዋና ዓላማው መሆኑን አውስተዋል ፡፡

በክልሉ በርካታ የጤና እክሎች እንደመኖራቸው በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ የሚደረጉ ምርምሮች ችግሩን በመለየት የመፍትሄ ሃሳቦች ቢያቀርቡም ወርደው ግን ተግባራዊ ሲደረጉ አናይም ፡፡ የዚህ ጉባኤም ዋና ዓላማ እስካሁን ምን ያህል ምርምሮች ተሰሩ ምን ያህሉስ ተተገበሩ የሚሉትን በመለየት መንግስታዊ ጤና ድርጅቶም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ጤና ተቋማት ተመራማሪዎች ለፍተው የሚያመጧቸውን ውጤቶች ተንተርሶ ወደ ተግባር መለወጥ በሚቻልበት ሁኔታ ለመወያየት ነው ብለዋል፡፡

በጉባዔውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ተመራማሪዎችን በማካተት፣ የአብክመ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ፣ የኢትዮዽያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ፣ የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እና ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የጤና ተመራማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ታድመዋል።

 

በጉባኤው የፎቶ አውደ ርዕይ የቀረበ ሲሆን ከ60 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ-BDU

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

Wisdom at the source of Blue Nile

Thank you for visiting BDU page!

ለተጨማሪመረጃዎች፡-

Telegram ፡- t.me/BDU_ISC_Official

Facebook: - https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube ፡- www.youtube.com/c/BduEduEt

LinkedIn ፡- www.linkedin.com/school/bahir-dar-university

Twitter: - https://twitter.com/bdueduet

Tiktok:-https://vm.tiktok.com/ZMLgRxdfL

website :- www.bdu.edu.et

#BDU60th_ANNIVERSARY