እንደ ቤተሰብ አባል

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን እንደ ቤተሰብ አባል ተቀበሉ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባሕር ዳር እንደቤቴ ፕሮግራሙ ተጨማሪ ተማሪዎችንና የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን በቤተሰብነት አገናኘ

 

የባሕር ዳር እንደቤቴ ፕሮጀክት ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ  ተማሪዎች ከባሕር ዳር ነዋሪዎች ጋር ቤተሰብአዊ ትስስር በመፍጠር  የባህል ልውውጥ እና ሰላማዊ የሆነ መማር ማስተማር እንዲኖር፣ዝምድና እና አንድነት  እንዲጠናከር በማድረግ ዩኒቨርሲቲዎችን ማዕከል በማድረግ  ይፈጠሩ የነበሩትን ግጭትና የግጭት ዝንባሌዎችን  ለመከላከል  ታልሞ የተቀረፀ ፕሮጀክት መሆኑን የሃሳቡ አመንጭ የሆኑት  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ አብራርተዋል። 

 

 የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን ወክለዉ የተገኙት ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አለባቸዉ  በበኩላቸዉ  ፕሮጀክቱ ሃገሪቱ ከገባችበት  ጥላቻና ግጭት ለመውጣት ጉልህ ድርሻ  እንዳለው በመግለፅ  ፕሮጀክቱ በሃገር ደረጃ ሊተገበር እንደሚገባው ጠቁመዋል። አቶ ባዩ የሃሳቡ ባለቤት የሆነዉን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን  ያመሰገኑ ሲሆን ከዚህ በኋላ በባለቤትነት ፈፃሚ መሆን ያለበት የከተማ አስተዳደሩና ህዝቡ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በማስቀጠልም  ፕሮጀክቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲካሄድና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ምን መደረግ አለበት? የህዝቡስ ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ አጭር ምክክር ከተደረገ በኋላ ተማሪዎች ከአዲስ ቤተሰቦቻቸው ጋር ትውውቅ በማድረክ የዕለቱ ዝግጅት ተጠናቋል።

 

ፕሮግራሙ በጥበብ  አዳራሽ  በኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ም/ ፕሬዚዳንት ፕሮግራም መሪነት የተጀመረ ሲሆን የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንትና ሌሎች ኃላፊዎች፣ የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የከተማይቱ  ነዋሪዎች እና ተማሪዎች ታድመውበታል።

 

የባሕር ዳር እንደቤቴ ፕሮጀክት ትልቅ ቤተሰብ ማፍራት የቻለና ተማሪዎችም ተመርቀው ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ከሄዱ በኋላ ባሕር ዳር ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር ቤተሰባዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው የቀጠሉ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡