በባሕር ዳር እንደቤቴ ተማሪዎች በገና በዓል

"በባር ዳር እንደቤቴ" ተማሪዎች የገናን በዓል ከባሕር ዳር ነዋሪዎች ጋር በደስታ አሳለፉ

በወንዳለ ድረስ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ "ባሕር ዳር እንደቤቴ" በሚል ስያሜ ተማሪዎች አመት በዓል ሲያከብሩ እንደቤታቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ በከተማው የሚገኙ ፈቃደኛ ወላጆች ጋር እንዲያከብሩ ሲደረግ ሁለት አመት ያስቆጠረ ሲሆን በ2013ዓ.ም የገና በዓልምን በባሕር ዳር ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር  በደስታ  አሳልፈዋል፡፡  

በዘንድሮው የገና በዓል 400 የሚሆኑ ተማሪዎች በከተማው ከሚገኙ ባላደራ ወላጆች ጋር  በዓሉን አብረው ያሳለፉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  እና የባሕር ዳር ወጣቶች አጋር አካላትን በማስተባበር  ሌሎች ከሶስት መቶ በላይ የሆኑ ተማሪዎችን በድብ አንበሳ ሆቴል በመቀበል ማዕድ ማጋራት መቻሉን የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ አደባባይ ጋሻው ገልፀውልናል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባሕር ዳር እንደቤቴ ፕሮግራምን ቀዳሚ በመሆን ከሁለት ዓመት በፊት የጀመረው ሲሆን  ሎሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሀሳቡን ወስደው እየተገበሩት ይገኛል፡፡ በቀጣይም ትምህርት ሚኒስቴር በሃላፊነት መንፈስ በአገሪቱ ባሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮውን ሊያሰፋው እንደሚገባ ተማሪ አደባባይ ጋሻው ጠቁሟል፡፡

ከባሕር ዳር እንደቤቴ ፕሮግራም አንድ ተማሪ ተቀብለው በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር ሲያሳልፉ ያገኘናቸው የባሕር ዳር ከተማ በም/ከንቲባ ማዕረግ የኢንዱስቲሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ አላዩ መኮነን አሁን ባለው ሁኔታ ባሕር ዳር እንደቤቴ ፕሮግራም ካሁን በፊት የነበረውን መተሳሰብ፣ ወዳጅነት እና መቻቻልን የሚያጠናክር ተምሳሌትነት ያለው በተግባር የታየ ትልቅ ሀሳብ ነው ብለዋል፡፡