ስፖርታዊ ውድድር

ለሁለት ወራት ሲካሄድ የነበረው ስፖርታዊ ውድድር ፍፃሜውን አገኘ 

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ጋር በጋራ በመሆን ከሚያዚያ 1 እስከ ግንቦት 30፣ 2013 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው የማህበረሰብ የውስጥ ስፖርት ውድድር ፍፃሜውን አገኘ፡፡

ውድድሩ ታራሚዎችን በስነ ምግባር እና በዕውቀት በማነፅ ውጤታማ፣ ተወዳዳሪ እና አምራች ዜጋን ለማፍራት አላማ አድርጐ ለ2 ወራት በ4 የስፖርት አይነቶች ሲካሄድ እንደነበር አዘጋጆች ጠቁመዋል፡፡

በፍፃሜው ውድድር በገመድ ጉተታ ዞን 1፣ በቫሊቮል ዞን 4፣ በእግር ኳስ ዞን 5 የተባሉ ማረሚያ ቤት ቡድኖች በጨዋታው አንደኛ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

የፍፃሜ መርሃ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤቶች የማረም፣ ማነፅ የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ግርማ ጥሩነህ ስፖርት አካዳሚው ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ የማህበረሰቡ አካል የሆኑትን ታራሚዎችን በስፖርታዊ ውድድር ማሳተፋቸው በስነ-ልቦና የጠነከረ ንቁ ዜጋን ከማፍራት አኳያ ፋይዳው የጐላ ነው ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዲን ዶ/ር ዳኛቸው ንግሩ ለአሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማት በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ስፖርት ለወዳጅነት፣ ለአንድነት እና ለፍቅር የሚያደርገውን እስተዋጽኦ ተገንዝበው ታራሚዎች ባሉበት ቦታ ስፖርታዊ ውድደሩ ያስፈልጋቸዋል በሚል ሀሳብ ላመነጩት ለመምህር ዳንኤል ጌትነት እና ለረዳት መምህር ጠቢቡ ሰለሞን እንዲሁም በግቢው በነበረው ቆይታ ለታራሚዎች እና ቅንነት፣ ፍቅርና አገልጋይነትን በተግባር ላሳዩት ለማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ውብሽት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም ውድድሩ በአራት የስፖርት አይነቶች በወንዶች ብቻ ለሁለት ወር መካሄዱን አውስተው በቀጣይ አመት በሴቶቸም ውድድሩን በማስቀጠል ለታራሚዎች የአንደኛ ደረጃ ስልጠና በመስጠት ስፖርቱ ቀጣይነት እንዲኖረው እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን በመወከል የተገኙት የፕሬዝዳንት  ጽ/ቤት  ኃላፊ  አቶ  አራጋው  ብዙዓለም  በበኩላቸው በዚህ መልኩ አሰፈላጊ ነው በሚል ስታደርጉት የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም እንደ ማህበረሰብ አገልግሎት ስፖርቱን ለመደገፍ ፍቃደኝነታችን እየገለፅን በእስካሁኑም ለደገፋችሁ ድርጅቶች ምስጋናየን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በሁለቱ ወራት ስፖርታዊ ውድድር የተሻለ አፈፃፀም ላደረጉ የቤንማስ እና አዲስ አምባ ሆቴልን ጨምሮ ለባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤቶች መምሪያ እንዲሁም ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ አመራሮችና ባለሙያዎች የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡