ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ በ2014 ዓ.ም የሚያከብረውን የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ አስመልከቶ ውይይት አካሄደ

*********************************************************************************************

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የኮሌጁ ማህበረሰብ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ሐምሌ 11-12/2013 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ  የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ  ዲን  የሆኑት ዶ/ር ታደሰ መለሰ የቀድሞው የባሕር ዳር መምህራን ኮሌጅ (አካዳሚ ኦፍ ፔዳጎጂ) በ1965 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር በዩኒስኮ እና በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ስምምነት እንደተቋቋመ እና በወቅቱም የመምህራን ትምህረት አካደሚ ይባል እንደነበር አውስተው ይህ አንጋፋ ኮሌጁ ከምስረታው ጀምሮ ያከናወናቸውን ስራዎች እና የኮሌጁን ታሪክ ለተተኪው ትውልድ ሰንዶ ማስቀመጥ ተገቢ መሆnuን ተናግረዋል፡፡

በመጭው ዓመት ኮሌጁ የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን እና ለዚህም የኮሌጁ አንጋፋ መምህራን ውይይቱ ላይ በሰጡት አስተያየት መሰረት የተለያዩ አራት ንዑስ ኮሚቴዎች ተመርጠዋል፡፡ የተመረጡት ኮሚቴዎች ኮሌጁ ከተመሰረተበት ዓመት ጀምሮ ያለውን ታሪክ ማዘጋጀትና መሰነድ፣ የኮሌጁን ታሪክ በዶክመንታሪ መልክ አዘጋጅቶ በዌብሳይት ማስቀመጥ እና በኮሌጃችን የተማሩ በሀገሪቱ ያሉ ታላላቅ ምሁራንን በ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮበልዮ ክብረ በዓል ላይ እንዲገኙ ማድረግ የሚሉ የስራ መርሃ-ግብር እንደተሰጣቸው ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ የልህቀት ማዕከል ሆኖ መመረጡን እንዲሁም  መምህራን የሚሰሯቸው የምርምር ስራዎች በተለያዬ ጊዜ በታዋቂ ጆርናሎች መታተማቸው ፣  የኮሌጁ ተመራማሪ መምህራን የሚሰሯቸውን የምርምር ስራ የሚታተሙበት ጆርናል አክርድቴሽን (እውቅና ያለው ጆርናል ኮሌጁ  እንዲኖረው) ማድረጉ  እንዲሁም ኮሌጁ 38ኛውን ዓመታዊ አለማቀፍ የግንቦት ሴሚናር በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑ በ2013 ዓ.ም ከተሰሩ ስራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ውይይት በኮሌጁን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ አንጋፋ መምህራን እና ሁሉም የኮሌጁ ማህበረሰብ ባሉበት ውይይት አድርጎ መስተካከል የሚገባቸው ነጥቦች ተስተካክለው ስትራቴጂክ እቅዱ ከአምስት ዓመት ወደ አስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ  ሆኖ እንዲዘጋጅ በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡

በኮሌጁ የሚያገለግሉ ነባር መምህራን እና  በያዝነው ዓመት ተቀጥረው ኮሌጁን የተቀላቀሉ አዳዲስ መምህራን እንዲሁም በተለያየ እርከን ላይ ሆነው የሚያገለግሉ  የአስተዳደር ሰራተኞችን ለመተዋወቅ እድል የፈጠረ የውይይት መድረክ በመሆኑ በዓመቱ መጨረሻ  ላይ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡