ሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ

የህግ ትምህርት ቤት ሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነፃ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከል “የተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ መብቶች ምንነትና አተገባበራቸዉ”  በሚል ርዕስ በባሕር ዳርና አካባቢዉ ለሚገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች አደረጃጀቶች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ሌሎች ተቋማት ለተውጣጡ ግለሰቦች በእንጅባራ ከተማ ከ28/08/2014 ዓም ጀምሮ የሁለት ቀን ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናዉም ስለሰብአዊ መብቶች በጠቅላላዉ ፣ ስለ ህፃናት ሰብአዊ መብቶች፣ ስለሴቶች ሰብአዊ መብቶች ፣ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች፣  ስለአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡

ስልጠናዉን በአካል በመገኘት በንግግር የከፈቱት የሕግ ትምህርት ቤቱ ዲን አቶ ተገኘ ዘርጋዉ በማሕበረሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ የተለያዩ አለመግባባቶችን ከችግሩ ምንጭ በመፍታትና ዘላቂነት ያለዉ መፍትሔ በመስጠት ረገድ የሐገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የማይተካ ሚና ያላቸዉ ሲሆን ይህ ሚናቸዉን ለማጎልበት የአቅም ግንባታ ጉዳዮች መሰጠቱ አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አያይዘዉም እነዚህ ተቋማት አለመግባባትን በሚፈቱበት ጊዜ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መብት ከግንዛቤ ዉስጥ ቢያስገቡ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲኖራቸዉና የተአማኒነት መጠናቸዉን እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ስልጠናዉ በሕግ ትምህርት ቤቱ የካበተ ልምድ ባላቸዉ አቶ ደሳለኝ ጥጋቡ እና አቶ ሙሃመድ ዳዉደ የተሰጠ ሲሆን ተስማሚ የሆነ  የስልጠና ስነዘዴ በመጠቀም በተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል፡፡

ሰልጣኞች በበኩላቸዉ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ስልጠና መሰጠቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳስገኘላቸዉ በመግለጽ በስልጠናዉ የጨበጡትን እዉቅት ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስልጠናዉ ቀጣይነት ባለዉ መንገድ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋል፡፡

ስልጠናዉ የተዘጋጀዉ በነፃ የህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከል አማካኝነት ነው