ምስለ ሕክምና ማሰልጠኛ

ምስለ ሕክምና ማሰልጠኛ ማዕከል ተከፈተ
******************************
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ሁለተኛ የሆነውን የምስለ ሕክምና ማዕከል አስመርቆ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰመመን (አንስቴዢያ) ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህርና የኢምፓክት አፍሪካ ተጠሪ የሆኑት አቶ ገብረሕይወት አስፋው በመከፈቻ ስነ ስርዓቱ ተገኝተው እንደተናገሩት ማዕከሉ የሰውን አካላዊ ባሕሪ ተላብሰው በተሠሩ አሻንጉሊቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ የተግባር ትምህርት የሚሰጥበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም የሕክምና ባለሙያዎች በዚህ ማሽን ልምምድ ሲያደርጉ ብቃታቸውን በተግባር እንዲፈትሹና በታካሚው ሊከሰት የሚችለውን ችግር ቀድመው እንዲገነዘቡ በማድረግ በራስ መተማመናቸውን ከፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የማዕከሉ መከፈት በዘርፉ ያለውን የባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ሰፊ እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል ፡፡
 
ማዕከሉ ‹‹ኢምፓክት አፍሪካ›› በተባለ ድርጅት አማካኝነት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት ገልፀው ፤ የማዕከሉ መቋቋም ለአጎራባች ክልሎች እና ዩኒቨርስቲዎች የአቅም ግንባታ በመስጠት የማስፋፋት ዕቅድ ይዟል ብለዋል፡፡
በአሜሪካው ቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል መምህርና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ባንታየሁ ስለሽ በበኩላቸው በሀገሪቱ ይህን መሰል አገልግሎት መሰጠት መጀመሩ ከባለሙያዎች ልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የሕክምና ስህተቶችን ለመቀነስ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
 
ሌላዋ መሳሪያውን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል በተግባር ለታዳሚው በማሳየት ላይ ያገኘናቸው አንስቴዢኦሎጂስት ህብስት ዘገየ እንደተናገሩት በንድፈ ሐሳብ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የሰመመን ሰጭ (አንስቴዢያ) ሕክምና በሰው አምሳያ በተሰሩ መሳሪያዎች በተግባር መታገዙ የእናቶችንና ህፃናት ሞት ለመቀነስ ጉልህ አስተዋፆ ያደርጋል ብለዋል፡፡
 
በምረቃ ስነ-ስርዓቱም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ ከሕክምናው ክፍል የተወጣጡ አስተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል ፡፡