ምረቃ

የተማሪዎች ምረቃ
===========
በሙሉጎጃም አንዱዓለም
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሀምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ፕሮፌሰር ተከስተ ዮሐንስ በክብር እንግድነት በተገኙበተት በደመቀ ስነ-ስርዓት አስመረቀ፡፡
በምረቃ ስነ-ስርአቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂዎች ለቤተሰቦቻቸውና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዚያት የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ለሀገሪቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ አክለውም በቅርቡ በተካሄደው አገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መታጨቱ በሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት ተመዝኖ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች የምርምር ውጤታቸው ምን ያህል ችግር ፈች እንደሆነና የማንን ተግዳሮት እንደፈታ እራሳቸውን እንዲጠይቁ፣ እንዲሁም በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ የኪነ- ሕንፃ (Architecture) ተመራቂዎች ውብ የህንጻ ዲዛይን እንደሚሰሩ እንደሚያውቁ የተናገሩት ፕሬዝደንቱ አባቶቻችን የሰሩትን የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን መጠገንን እንዲያስቡትና የሀገሪቱን ጉልህ ችግር እንዲቀርፉ አሳስበው የወደፊት ህይወታቸው የተቃና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳው የኢትዮጲያ የሳይንስ አካዳሚ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ተመራቂዎች የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለዚህ መብቃታቸው ያላቸውን ፅናት እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በማስከተል ዩኒቨርሲቲው በአገር አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎችን የመለየት ስራ በቅርቡ ተካሂዶ የላቀ ውጤት በማስመዝገቡ ግዙፍነቱን ያስመሰከረ እንደሆነ ተናግረው የዕለቱን ምረቃ ልዩ የሚያደርገው አገር አቀፍ የምርጫ ስርዓት ያለምንን ተግዳሮት በተከናወነበት ማግስትና የታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሚከናወንበት ወቅት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች የትምህርቱን ዓለም ጉዞ ጨርሰው ወደ ስራው ዓለም የሚሽቀዳደሙበት ወቅት ላይ በመሆናቸው ባካበቱት እውቀትና ክህሎት ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ በአደራ መልክ ቁልፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የምረቃውን ስነ ስርዓት ያስፈፀሙት የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራርና አልሙናይ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ፀጋየ ሲሆኑ ተመራቂዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የተማሩ 725 ሴት እና 1638 ወንድ በድምሩ 2363 መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከነዚህ መካከል በተለያየ ምክንያት ምረቃቸው የዘገየ 6 ተመራቂዎችን ጨምሮ 28ቱ የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በመርሀ-ግብሩ ላይ በምርምር ስራቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የድህረ ምረቃ ተመራቂዎች በክብር እንግዳውና በዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች የእውቅናና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ሁሉም የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎችም መድረክ ላይ በመቅረብ የምረቃ ስነ ስርዓታቸውን አከናውነዋል፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪ የኪነ- ሕንፃ (Architecture) የትምህርት ዓይነት ከተመረቁት መካከል እጩ ተመራቂ ገሊላ ተመስገን 3.5 አማካይ ውጤት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
በምረቃ ስነ-ስርአቱ የአማራ ክልል የፖሊስ ማርሽ ባንድ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችንና የሰልፍ ትሪኢቶችን ያቀረበ ሲሆን የፖሊስ የሙዚቃ ባንዱም የእንኳን ደስ አላችሁ እና ሌሎች አዝናኝ ሙዚቃዎችን አቅርቧል፡፡