መማር ማስተማሩን በቴክኖሎጂ

መማር ማስተማሩን በቴክኖሎጂ የማዘመን ተግባር

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ከዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው መምህራን ለ3 ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ግቢዎች የ "Smart Board" አጠቃቀም ስልጠና አካሄደ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አበበ መማር ማስተማሩን ቀላል፣ፈጣንና ዘመናዊ ለማድረግ የካበተ ልምድ ባላቸው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ባለሙያዎች ስልጠናው መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

በስልጠናው 321 የ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ለሚያስተምሩ መምህራን ቅድሚያ በመስጠት የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ለሁሉም መምህራን በሁሉም ግቢዎች እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

ከአሰልጣኞች መካከል የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ማሩ የስልጠናው ዋና ዓላማ ዘመኑ የዲጂታል ስለሆነ መማር ማስተማሩን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ጥራቱንና ተደራሽነቱን ለማጎልበት ታልሞ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም መማር ማስተማሩን ለማዘመን የተሻለ ቴክኖሎጂ እንዲተገበር በማድረግ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ግቢዎች 75 "Smart Board" መገጠማቸውንና በዚያው ልክ ክፍሎቹ ፅዱ፣ማራኪና የተለያዩ አስፈላጊ ነገሮች የተገጠመላቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

ስማርት ቦርዶች ("Smart Board") አንድ መምህር በሚያስተምርበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በኬብሎች አማካኝነት ከላብቶፕ፣ከኢንተርኔትና ከሌሎች ቴክኖሎጅዎች ጋር በማገናኘት ወይም የሚፈልገውን በመፃፍ ማስተማር እንደሚችል በስልጠናው ግንዛቤ ለመፍጠር ተችሏል፡፡

                                                          በሙሉጎጃም አንዱዓለም