ለዳኞች ስልጠና ተሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ለዳኞች ስልጠና ሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በባህር ዳር እና ዙሪያዉ ለሚገኙ የሶስት ወረዳ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ከሰኔ 5 ጀምሮ በእንጅባራ ከተማ ስልጠና ሰጠ፡፡

የተሰጠዉ ስልጠና በወንጀለኛ ስነ-ስርዓት ሕግ እና በማስረጃ ሕግ ዙሪያ ሲሆን በስልጠናዉ ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ወረዳ ፍርድ ቤት፣ ከጎንጅ ቆለላ እና ከአዴት ወረዳ የተወጣጡ 35 ሰብሳቢ ዳኞችና ዳኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በስልጠናዉ የሕግ ትምህርት ቤቱ ዲን የእንኳን ደሕና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸዉም ፍርድ ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ዘብ እና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዋስትና ስለሆኑ የሕግ የበላይነት እና የፍትህን ተደራሽ የማረጋገጥ  ሚናቸዉን በተገቢዉ መንገድ መወጣት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡ የስልጠናዉ ግብ ሙሉ በሙሉ  ሊሳካ የሚችለዉ ዳኞች በስልጠናዉ ያገኙትን እዉቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ለመተግበር ጥረት ማድረግ ሲጀምሩ ስለሆነ በስልጠናዉ የምታገኙት እዉቀት፣ ክህሎትና ልምድ በተግባር መተርጎም ይኖርባቸኋል በማለት አሳስበዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳርና አካባበዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት አቶ ኃይለየሱስ የሕግ ትምህርት ቤቶች በአካባቢዉ ከሚገኙ የፍትህ አካላት እጅና ጓንት ሆነዉ መስራት የሚገባቸዉ መሆኑን ጠቅሰዉ በምርምር፣ በአቅም ግንባታ ስልጠና፣ እና አጋርነቶችን በመፍጠር በፍትህ ስርዓቱ ላይ መጫወት የሚገባቸዉን ሚና በተገቢዉ መንገድ መወጣትና በቀጣይም ይህንን እና መሰል ተግባራትን አጠናክረዉ መቀጠል እንደሚኖርባቸዉ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ ስልጠናዉን የሰጡት የህግ ትምህርት ቤቱ አንጋፋ መምህር ረ/ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ ሲሆኑ ስልጠናዉ በሕጉ አተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እና ሕጉ በምን አግባብ መተርጎም አለብት የሚለዉን  ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር አስተሳስረዉ ለፍርድ ቤቶቹ የወደፊት ስራ በሚጠቅም መንገድ አቅርበውታል፡፡

ስልጠናዉን የተካፈሉት ዳኞች እና ሰብሳቢ ዳኞች በስልጠናዉ ለወደፊቱ ስራቸዉ የሚጠቅም አስተማሪ ግብአትና ጠቃሚ ትምህርት ማግኘታቸዉን ጠቅሰዉ አሰልጣኙንና የሕግ ትምህርት ቤቱን አመስግነዋል፡፡ አስተያየት ሰጭዎች አክለውም የሕግ ትምህርት ቤቱ ለወደፊቱ የተለያዩ የአቅም ግንባታ እንዲሰራና ጅምሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡