ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ገለፃ ተደረገ

ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ገለፃ ተደረገላቸው

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ሚኒስተር የተመደቡለትን የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች በሰላም ግቢ ፋሽን አዳራሽ ስለቤተ መጻሕፍት አጠቃቀም በዳይሬክተሩ አቶ አሰማኸኝ አያሌው፣ ተማሪዎች ስለ ሚያጋጥማቸው የስነ ልቦና እና ማህበራዊ ጫና  በተማሪዎች  አማካሪ ማዕከል  አስተባባሪ  ዶ/ር አብዮት የኔዓለም፤ ለተማሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ሙላት ስሜ ገለፃ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ተማሪዎች የሬጅስትራርን የጊዜ ሰሌዳ ተጠቅመው የወጣውን ሕግና ደንብ እንዲያከብሩ በዩኒቨርሲቲው  ማዕከላዊ ሬጅስትራር  ቡድን  መሪ በአቶ መላኩ ቢያዝን  ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡

በሰላም ግቢ ስለተመደቡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች አቀባበል የጠየቅናቸው የጀማሪ ተማሪዎች መርሃ ግብር የሰላም ግቢ ምክትል ዲን አቶ  ደምሰው መንግስቴ  በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ1300 በላይ የማህበራዊ እና  የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መካከል ከ700 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በአካል መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ አንድ ተማሪ በአንድ ወሰነ ትምህርት ከ85% በላይ የሆነውን ክፍለ ጊዜ በክፍል ወስጥ ተገኝቶ  መከታተል ይኖርበታል በዚህም ከአላስፈላጊ ውጣ ውረዶች ይድናል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  አስተዳደር  ጉዳዮች ተቀዳሚ ዳይሬክተር አቶ ገደፋው ሽፈራው አንጋፋውና የመጀመሪያው  የምርምር  ዩኒቨርሲቲን መርጣችሁ በመምጣታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ኃላፊው አታርፍድ በሚል ለተማሪዎች ባቀረቡት ፅሁፍ የህይወት  ትልቁ ስህተት  ማርፈድ ነው፤ ሁሉም ነገር የሚያምረው እና የሚበጀው በጊዜው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ማድረግ ያለብህን ነገር  ሳታመነታ ተሎ አድርገው፣ መጀመር ያለብህን ጉዳይ ሳትዘገይ ጀምረው፣ መተው ያለብህ ነገር ሳታቅማማ በጊዜ ተወው፣ መወሰን ያለብህ ጉዳይ ካለም ዛሬውኑ ወስን፣ ማቋረጥ ያለብህ ግንኙነት ካለ ሳይወሳሰብ ቋጨው፤ ህይወት ማለት እንደ አልፎ ሂያጅ ወንዝ ናት ወደፊት እንጂ ወደኋላ አትራመድም፣ እረፍዶ እንዳይፀፅትህ ጊዜህንና እድሜህን ባግባቡ ተጠቀምበት አስተውል ፀፀት መጨረሻ  እንጂ መጀመሪያ  መጥቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ነገን እንዳይቆጭህ ዛሬ አታርፍድ በሚል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡