ህዝበ ገለጻ ኢኮኖሚያዊ ክህሎትን ለማሳደግ ...

ትምህርት እና የምርምር ተወዳዳሪነት ኢኮኖሚያዊ ክህሎትን ከማሳደግ አኳያ በሚል ርእሰ ጉዳይ ህዝበ ገለጻ ተካሄደ

**********************************************************************

[ሚያዚያ 28/2014ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ] 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል  ለአካዳሚክ እና ለምርምር ተወዳዳሪነት ኢኮኖሚያዊ ክህሎትን ማሳደግ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ህዝበ ገለጻ በኮሌጁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለባቸው አስፋው በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው  የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር  ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና  ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት ከዚህ በፊት በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ላይ የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማቋቋም ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በዛሬው እለት ህዝበ ገለጻ የሚያደረጉት ዶ/ር ግርማ ተስፋሁን ከዚህ በፊትም ስልጠና ሰጥተውልን ያውቃሉ ዛሬም ስለመጡ አመሰግናለሁ ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ፡፡

የአገራችን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በእውቀትና ጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ በየዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራ አይደለም ስለሆነም በትኩረት መሰራት ይገባል፡፡ እንደሀገር የኢኮኖሚ ፍኖተ-ካርታችን ዝብርቅርቅ ያለ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ስለሆነም የኢኮኖሚ አቅም የት አካባቢ ነው ያለው ብሎ ያሉንን ጸጋዎች በመለየት ጥናትና ምርምር ማድረግ አለብን፡፡ ውሃ እና አፈር በእጃችን ይዘን ተመጽዋች የሆንበት ሁኔታን መቀየር አለብን፤ ለኢንዱስትሪ ግብአቶች የሚሆኑ ምርቶች በስፋት እንዲመረቱ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ መሰራት ይገባል ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም በዚህ ክልል ያልተጠቀምንባቸው የኢኮኖሚ አቅሞች በየቦታው አሉ እነሱን አውጥተን ጥቅም ላይ ለማዋል የዩኒቨርሲቲው አመራርና ትምህርት ክፍሉ ለምን የኢኮኖሚክስ ምርምር ማዕከል አቋቁመን በትኩረት አንሰራም የሚል ቁጭት ሊያድርብን ይገባል፡፡

የኢኮኖሚክስ ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ያሉ ሰዎች ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ዛሬም የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ጠንክሮ ለመስራት የነደፋቸው ፕሮግራሞች አበረታች ናቸው የተዘጋጁት መርሀ-ግብሮችም ለሌሎች ትምህርት ክፍሎች ጭምር ልምድና ተሞክሮ የሚሰጥ ነው ይህም መጠናከር አለበት ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የኢኮኖሚ ምርምር ማእከሉን እንድታጠናክሩት ከአደራ ጭምር ማሳሰብ እፈልጋለሁ ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ፡፡

ህዝበ ገለጻውን ያደረጉት ዶ/ር ግርማ ተስፋሁን  ለአካዳሚክ እና  ለምርምር  ተወዳዳሪነት  ኢኮኖሚያዊ ክህሎትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በዝርዝር ገልጸዋል፡፡

የመርሀ ግብሩ ዋና አስተባባሪ እና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ አቶ ነጋ እጅጉ በበኩላቸው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ድረስ የኢኮኖሚክስ ሳምንት በሚል የተለያዩ ስልጠናዎችን፤ ህዝባዊ ገለጻዎችን፤ የPhD ተማሪዎችን ተቋቁሞ የመሳሰሉ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን በተለይም የPhD ተማሪዎች በህዝበ ገለጻው ያገኙትን እውቀት ከስልጠናው ጋር አስተሳስረው ይጠቀሙበታል ብለዋል፡፡

ህዝበ ገለጻው ትኩረት የሚያደርገው በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ትምህርት የተለመደና ለምርምር ግብአት የሚሆን የኢኮኖሜትሪክስ ሞዴልን ጠቀሜታ ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ይህን ሞዴል በምን አይነት መንገድ መጠቀም ውጤታማ እንደሚያደርግ እንዲሁም ኢኮኖሜትሪክስ ያለውን ጠቀሜታ በትክክል ተረድቶና እሱን ተጠቅሞ ጥናትና ምርምር ሰርቶ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆን ጥናት እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል አቶ ነጋ እጅጉ፡፡

ሌሎች ትምህርት ክፍሎችም ተመሳሳይ ስራዎችን መስራት ቢችሉ ሲሉ አቶ ነጋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፤ የ PhD ተማሪዎች፤ የኮሌጁ መምህራን፤ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ PhD ተማሪዎች፤ከአማራ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች የመጡ ተሳታፊዎች በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡