የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን ስፖርት ለማሳደግ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ መሆኑ ተነገረ

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተዳከመ የመጣውን የእግር ኳስ ስፖርትን ጨምሮ በአትሌቲክስ እና በሌሎችም የስፖርት አይነቶች ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች በሚል ምድብ ታዳጊዎችን ለማሰልጠን ከሦስት ወር በፊት ለታዳጊዎች ይፋዊ ጥሪ አውጥቶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ባሕር ዳር ከተማ ካሉ ትምህርት ቤቶት የተወጣጡ እና ተሰጥኦ ያለቸውን በርካታ ታዳጊዎችን በፕሮጀክት አቅፎ በዩኒቨርሲቲው የስፖርት አካዳሚ ሲያሰለጥናቸው መቆየቱ ይታወቃል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በዝግጅቱ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ባስገነባው ሁለገብ የስፖርት አካዳሚ ክህሎት ያለቸው ታዳጊዎች በአካዳሚው የስፖርት መምህራን ታግዘው መሰልጠናቸው ምን አልባት አሁን እየተዳከመ የመጣውን የእግር ኳስ ስፖርት እንዲያንሰራራ የበኩሉን እነደሚያበረክት ገልፀው ለሀገርም ከፍተኛ ኩራት የሚሆኑ ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚቻል እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ፍሬው አክለውም ይህ እውን የሚሆነው የታዳጊ ህፃናት ጥረት ሳይንሰዊ በሆነ ስልጠና ሲታገዝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ደግሞ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ መምህራን እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊውን የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ለኢትዩጵያ የስፖርት የሚጠበቀውን ማበርከት እንደሚቻ ገልፀዋል፡፡

የአማራ ስፖርት ኮሚሽን የተሳትፎ ስልጠና ውድድር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ምትኩ አክሊሉ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እነዚህን ታዳጊዎች እና ከ50 በላይ የሚሆኑ የአትሌቲክስ ሰልጣኞችን ለማሰልጠን እየወሰደ ያለውን ኃላፊነት አድንቀው እየተዳከመ ያለውን ስፖርት ለመታግ ብሎም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋፃ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም በክልላችን ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን አርአያ በመከተል ለሀገራችን ስፖርት ማደግ የበኩላቸውን አስተዋፆ እንዲያደርጉ ጠቁመው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሚያደርገው በጎ እንቅስቃሴ የአማራ ስፖርት ኮሚሽን ከጎኑ በመሆኑን አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዲን ዶ/ር ተስፋዬ ደሳለኝ በበኩላቸው ስልጠናው በእለቱ የተመለመሉትን ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችን እና ከሦስት አመት በፊት በዩኒቨርሲቲው እገዛ እየሰለጠኑ ያሉትን ከ50 በላይ የሚሆኑ የአትሌቲክስ ሰልጣኞች በይፋ በዩኒቨርሲቲው ታቅፈው አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡

በእለቱ በባሕር ዳር ከተማ ለረጅም አመታት የሴቶችን የቅርጫት ኳስ ቡድን ሲደግፉ የነበሩት አቶ በለጠ ለሚያሰለጥኑት ቡድን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እውቅና በመስጠት የቁምጣና የማሊያ ሽልማት ተበርክቷል፡፡በመጨረሻም በፕሮጀክቱ ለታቀፉ ለሁሉም ታዳጊ ህፃናት የቁምጣና የማሊያ ሽልማት በባሕር ዳር ዩኒቨርርሲቲ ፕሬዚዳንት በዶ/ር ፍሬው ተገኘ እጅ ተረክበዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደን ጨምሮ አሰልጣኝ መምህራን ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን የመጡ የሚመለከታቸው አካላት እና ሌሎች ተገኝተዋል፡፡