በ2012 ዓ.ም ለተመደቡ አዲስ ተማሪዎች አቀባበል

በዩኒቨርሲቲው ለተመደቡ አዲስ ተማሪዎች የሞቀ አቀባበል ተደረገላቸው!!

በሙሉጌታ ዘለቀ

በ2012 ዓ.ም ለተመደቡ አዲስ  ተማሪዎች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በዋናው ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ትምህርት ለመቅሰም የተሰባሰቡ አዲስ ተማሪዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ እነዚህን አዲስ ተማሪዎች ለመቀበል ደፋቀና ያሉ የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችን እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላትን አመስግነዋል፡፡ ተማሪዎች ከወላጅ ቤተሰቦቻቸው ርቀው ይምጡ እንጂ በተጨባጭ ግን ወደሌላኛው ቤታቸው ወይም ወደ ወገናቸው፣ ወንድም እህታቸው የመጡ መሆናቸውን መገንዘብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡  

ዶ/ር ዘውዱ አክለውም ዛሬ ዓለም የኋላቀርነት ምልክት አድርጎ የተጠየፈውን የመለያየት በሽታ እኛ ኢትዮጵያዊያንን በማይመጥነን ደረጃ ወርደን ከመቀራረብና በትግሮቻችን ላይ ከመነጋገር  ይልቅ ስለሰፈር ማሰብ ጀምረናል፡፡ ያም ሆነ ይህ የሁሉም ችግሮቻችን መፍቻ እውቀትና ክህሎት ማመንጫ የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን የነዚህ የወረዱ አመለካከቶች ማራመጃ መሆን እንደሌለባቸው በአፅኖት ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዘውዱ በንግግራቸው መቋጫም እኛ ተማሪዎች ነን እንማር እንወቅ ፣ያልገባንን እንጠይቅ፣ የሚጠቅመንን ለይተን እንያዝ፣ እኔ የተሻልኩ ነኝ የሚል ቢኖር ነውር ነገር ባለማድረግ መሻሉን ያሳይ እሳት በውሃ እንጂ በእሳት አይጠፋም ክፉውን ነገር በክፉ ከመፍታት ይልቅ በበጎ መፍታት ባህላችን እናድርግ በማለት ተማሪዎች በጋራ ለመማማር ብቻ እዲሰለፉ መክረው  ዓመቱ መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን  አስተላልፈዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በ2012 ዓ.ም. ለተመደቡ አዲስ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ደረጃ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ያለ ትልቅ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም እንደማሳያ በሀገራችን ካሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያልተካተተ/የማይሰጥ የማሪታይም አካዳሚ ከፍቶ ከ1500 በላይ ተማሪዎችን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ስምና ዝና ያገኘ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር ፍሬው አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እሴቶች ፡- ዕውቀትን እና ጥበብን ፍለጋ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን የልዕቀት ማዕከል ማድረግ፣ ብዝሀነትን ማክበር፣ አለማቀፋዊነት እና ህብረተሰብን ማገዝና መደገፍ ለተማሪዎች አብራርተዋል፡፡ በንግግራቸው ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው ጥላቻን ከሚፈጥሩ ማንኛውም ነገር ተቆጥበው የዩኒቨርሲቲውን ህግና ደንብ አክብረው ትምህረታቸውን እንዲማሩ አሳስበዋል፡፡

 የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ መምህርና የወልደያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ ለአዲስ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እኪገቡ ያለውን የሂዎት ውጣውረድና ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ያጋጠማቸውን የሂዎት ተሞክሮዎቻቸውን ለተማሪዎች አካፍለዋል፡፡ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ብቻ የሚያገለግል መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ያለው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተማሪዎች ብዙ ውጣውረድና ፈተናውችን በማለፍ ስኬት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ አለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለችበት ሰዓት  በዘርና በቋንቋ ከሚከፋፍሉ እኩይ ባህሪ ካላቸው ግለሰቦች እራሳቸውን በመጠበቅ ለቤተሰብ እንዲሁም ለሀገር የሚበጅ እውቀት ይዘው እንዲወጡ መክረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዩች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብረሀኑ ገድፍ ለተማሪዎች በግቢ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ በሚያገኟቸው የምግብ፣ የመኝታ፣የውሃ፣ የመብራት፣ የመዝናኛ እና ሌሎችም አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ አሟልቶ ለተማሪዎች ለማቅረብ ደፋ ቀና ሲል መቆየቱን ጠቅሰው ማንኛውም ተማሪ በምንሰጣቸው አገልግሎቶት የጥራት ማነስ ቢኖር እንኳን በመነጋገር ችግሮችን እንደሚፈቱ አቶ ብርሀኑ ተናግረዋል፡፡ የአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ ፆታ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ብርሃኔ መንግቴ ለአዲስ ተማሪዎች ማንኛውንም ችግር ሲገጥቸው በሁሉም ግቢዎች በተቋቋሙት የስርዓተ-ፆታ ቢሮዎች መገልገል እንደሚችሉ ተናግረው በተለይ አዲስ ለተለመደቡ ተማሪዎች በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የህይወት ክህሎት ስልጠና እደሚሰጥና ስልጠናውንም ሁሉም አዲስ ተማሪዎች እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የሆነው ተማሪ አደባባይ ጋሻው እንዳለው  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት የተማሪዎችን መብት በማስጠበቅ በአገልግሎት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ይፈታል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ተማሪ ሰላምን ከማይወዱና የተለዬ አላማ አንግበው ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይሆኑና ትምህርታቸው ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡