አውደ ጥናት

ሰባተኛው የአማርኛ ቋንቋና የባህል ዘርፎች አገር አቀፍ አውደ ጥናት በዩኒቨርሲቲው ተካሄደ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም (አቋማተ) ሰባተኛውን የአማርኛ ቋንቋና የባህል ዘርፎች አገር አቀፍ አውደ ጥናት መጋቢት 6 2011 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ፔዳ ግቢ አካሄደ፡፡ መርሃ-ግብሩ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና ለፕሮግራሙ አዘጋጆች የምስጋና መልዕክታቸውን አስተላልፈው አማርኛ ቋንቋን ከዘመኑ ጋር ለማስኬድና ከአገር አቀፍ ደረጃ በዘለለ መልኩ ለአፍሪካ ህብረት የመግባቢያ ቋንቋ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው ከማዕከሉ ጋር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ አክለውም በአሁኑ ወቅት አማርኛ ቋንቋንና ባህልን ለማበልፀግ የሚያግዝ “ Online Dictionary” እና የመማሪያ “Application” ስለሌለ ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በግንባር ቀደምትነት መስራት እንዳለበት በአንክሮ ተናግረው የአውደ ጥናቱ መካሄድም የተጠቀሱትንና መሰል ክፍተቶች ለመሙላት የማንቂያ ደወል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የዓውደ ጥናቱን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከሰጣቸው ስድስቱ እንቁ ሙህራን አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ “ቋንቋ የሰው ሰውነት ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተነስተው የቋንቋ መስፋፋት ከግለሰብ ጀምሮ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ፣አገር እንደ አገር እንዲያድግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውና የበሰለ ቋንቋ ከሌለ ሀሳብም እንደሚቀጭጭ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በማስከተል የሰው ልጅና የቋንቋ ትስስር ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው በማስረጃ አስደግፈው ሰፊ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ሳይንሳዊ ቋንቋ መጠቀም ደረጃን ከፍ ሲያደርግ የሳሳ ቋንቋና የወረደ ቃላት መጠቀም ደግሞ በአንፃሩ የእውቀትን ዲካ ስለሚለካ የአውደ ጥናቱ ዓላማ የቋንቋን እድገት ለማምጣትና ባህልን ለማስተዋወቅ የሚጠቁሙ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ቋንቋችንና ባህላችን ያሉበትን ሁኔታ አብጠርጥረው በማሳየት አንዱ ከአንዱ የእውቀት ሽግግር የሚያደርግበት መድረክ እንደሚሆን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች በተለያዩ ምሁራን ቀርበው በቀረቡት ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡