ወደ አረንጓዴ መንደር ምስረታ

በሙሉጉጃም አንዱዓለም

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ብሉ ናይል ውሃ ኢንስቲትዩት ስር የሚገኘው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ መንደር መመስረት (Climate Smart Villages/CSV/) የተሰኘው ፕሮጀክት በገጠር ልማት ላይ ለመስራት ስምምነቱን በዩኒቨርሲቲው ጥበብ ህንፃ አዳራሽ አሳወቀ፡፡

የመክፈቻ ንግግሩን ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶ/ር የሻንበል መኩሪያው ሲሆኑ ፕሮጀክቱ ሊሰራ ያሰበው አኩሪ ተግባር በመሆኑ በወረቀት ላይ ያለው ተግባራዊ ሆኖ እንዲታይ አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ፕሮጀክቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሰበሰባቸውን ተሞክሮዎች ያካተቱ የተለያዩ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ የታለመው ንድፈ ሀሳብ ወደ ተግባር ተለውጦ ይታይ ዘንድ ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ጀምሮ ሁሉም የሚመለከተው አካል ርብርብ ማድረግ እንደሚገው የፕሮጀክቱ ባለቤቶችና በሙያው የተካኑ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

በእለቱም የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች ከተለዩ በኋላ ተግባራዊ እንቅስቃሴውንም ተጨባጭ ለማድረግ የስራ ድርሻ ክፍፍል ተደርጓል፡፡