የስፔሻሊስት ሐኪሞች ስምሪት ለወገን አለኝታነት

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ጊዎን ሆስፒታል ያሰለጠናቸውን ስፔሻሊስት ሐኪሞች በክልሉ የተለያየ ሆስፒታሎች የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ አሰማራ፡፡

ለአንድ አመት የሚቆየው ይህ የሐኪሞች ስምሪት በክልሉ በተለይም በባሕር ዳር አካባቢ በጥበበ ጊዎንና በፈለገ ሕይወት ሆስፒታሎች ያለውን የስራ ጫና ለመቀነስና ታካሚዎችም ርቀው ሳይጓዙ በአቅራቢያቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የጥበበ ጊዎን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ተቀዳሚ ዳይሬክተር ፐሮፌሰር የሺጌታ ገላው ከመጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ ሃኪሞችን ወደ ተለያዩ ሆስፒታሎች የመላክ ተሞክሮ እንደነበረ ገልጠው ወደፊትም ይህን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡ 
በዚህ ዙር 13 የሚደርሱ ስፔሻሊስት ሐኪሞች የተሰማሩ ሲሆን ስድስት የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና እና ሰባት የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሓኪሞች መሆናቸው ተገልጧል፡፡ እነዚህም ሐኪሞች ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገር የበለጠ አገልግሎት ወደሚሰጡበት ምዕ/ጎጃም፣ ምስ/ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋና አዊ ዞኖች የተመደቡ ናቸው፡፡

በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የጤና ቢሮ ተወካይ አቶ አበበ ከህክምናውም ባሻገር ጥሩ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት በቆይታቸው ለውጥ እንዲያመጡ አደራ ብለዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘም ለሃኪሞቹ ባስተላለፉት መልዕክት የሙያውን ክብር በመጠበቅ ማህበረሰባችን የሚጠብቀውን የህክምና አገልግሎት ከመልካም ሙያዊ ስነ ምግባር ጋር በማጣመር አርዓያነት ያለው ተግባር ፈጽመው በመመለስ የራሳቸውንም ሆነ የተቋማቸውን ስም በበጎ እንዲያስጠሩ በማሳሰብ የግል ተሞክሯቸውንም ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡ የተለያዩ እንግዶች ምስጉን ሐኪሞችና የሐኪሞቹ አሰልጣኝ መምህራን በተገኙበት ስነ-ስርአት ላይ ከሐኪሞቹም የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን በመጨረሻም ፕሬዚደንቱ የማስታወሻ ስጦታ ለተጓዥ ሀኪሞች አበርክተዋል፡፡