ኮሌጁ ስድስተኛውን ዓመታዊ ኮንፈረንስ አካሄደ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ ስድስተኛውን ዓመታዊ ኮንፈረንስ በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሸ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አካሄደ::

መርሃ-ግብሩ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የፕሮግራሙ የክብር እንግዳና የአብክመ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ኮምሽነር ዶ/ር ሰብስበው አጥቃው ሲሆኑ ሳይንስ የሁሉም ነገር መሰረት እንደመሆኑ መጠን በዘመነ መልኩ ለመተግበር የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ስለሚገባቸው የኮንፍረንሱ መካሄድ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልፀው የሚሰሩ የምርምር ውጤቶች ሽልፍ ላይ ብቻ ሳይቀመጡ የህብረተሰቡን አንኳር ችግር ነቅሶ በማውጣትና የምርምሩን ስነ-ምግባር በመከተል መሬት የነካ ስራ እንዲሰራ ተቋማቸው ክትትልና ቁጥጥሩን የማስረፅ ተግባር እንደሚያከናውን አስገንዝበዋል፡፡

የኮንፍረንሱን ቁልፍ መልዕክት(Keynote Speech) ያስተላለፉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ናቸው፡፡ሳይንሳዊ ግኝቶችን በተግባር ማዋል የበለፀጉ አገራት መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ምርምሮችን ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎች ቅንጅት ስለሚያስፈልግ በኮንፍረንሱ አማካኝነት በሚቀርቡት ፅሁፎች መነሻነት የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን በማየት ክፍተቶችን ከመሙላት አንፃር በር ከፋች መሆኑን ገልፀው በየጊዜው የሚቀርቡትን የምርምር ውጤቶች ተከታትሎ የማስፈፀምና ፖሊሲ እስከ ማስቀየር የሚደርሱትን የመከታተል ክፍተት የነበረ ቢሆንም ለወደፊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ደለለ ወርቁም በበኩላቸው ለመላው ታዳሚ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ኮሌጁ አንጋፋና በርካታ አኩሪ ተግባራትን የሚያከናውን መሆኖን በሰፊው አስተዋውቀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ የአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ ሙህራን የቀረቡ ሲሆን የኮሌጁ ቤተ-ሙከራና የተለያዩ ግቢዎች ተጎብኝተዋል፡፡