የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አምስተኛውን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቦርድ በ07/01/2010 ባደረገው ስብሰባ የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ ለሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ቢሻው አምስተኛውን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት በመላው የዩኒቨርሰቲው ማህበረሰብ ስም አምስተኛውን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት ላገኙት ለፕሮፌሰር አለማየሁ ቢሻው “እንኳን ደስ አለዎት!” እያለ የደረጃ እድገቱ በዩኒቨርሰቲው እየተከናወነ ላለው ተቋማዊ ለውጥ ስኬት ፋና ወጊ በመሆኑ የተሰማውን ደስታ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ፕሮፌሰር አለማየሁ ቢሻው በትምህርት እና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በኮሌጁ እና በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙ ምሁር ናቸው፡፡ በመሆኑም ከመማር ማስተማሩ ጐን ለጐን ከ32 በላይ ችግር ፈች የሆኑ የምርምር ሥራዎችን በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ጆርናሎች በማሳተም ለሀገርና ለወገናቸው አበርክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 13 ያልታተሙ ምርምሮችን እና 4 የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አለማየሁ ቢሻው ሌሎች ለዕድገቱ የሚጠየቁ መስፈርቶችን ከምርምር ሥራዎቻቸው ጎን ለጎን በተሰጣቸው ኃላፊነት ሁሉ በመግባት የድህርምረቃ ጥናት ዲን፣ የፕሬዘዳንት ጽ/ቤት ሃላፌ፣የባሕር ዳር ኢዱኬሽን ጆርናል ዋና ኢዲተር፣ የስርዓተ ትምህርት ፒኤችዲ ፕሮግራም መሪ፣ የፕላኒንግ ኦፊሰር፣ የርቀት ትምህርት አስተባባሪ፣ የተማሪዎች ዲን፣ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ በመሆን የሰሩ እና በሌሎች የተለያዩ የኮሚቴ ስራዎችም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍም በሙያቸው በርካታ አገልግሎቶችን በመስጠት ሀገርና ወገን የሚጠቅም ሥራ እያበረከቱ ያሉ ምሁር መሆናቸውን በመገንዘብ ጭምር ነው የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሙሉ ኘሮፌሰርነት የማዕረግ እድገት የሰጣቸው፡፡