የመምህራን ቀን

“ሀገሩን የሚወድ፣ ልዩነቶችን አክብሮ አንድነታችንን የሚቀበል፣ በስነ-ምግባር የታነፀ እና ግብረገብነት ያለው ትውልድን ለመፍጠር  መምህራን የላቀ ድርሻ አላቸው”  ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር 

 

 

 በሙሉጌታ ዘለቀ

 

 

“መምህራን ቀውስ ለመቀልበስም ሆነ ለመጭው ጊዜ ብሩህነት ግንባር ቀደም ሚና አላቸው “  በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የመምህራን ቀን አስመልክቶ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የነበረውን የማጠቃለያ የውይይት መርሃ-ግብር  አጠናቀቀ፡፡ 

 

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን የገፅ ለገፅ ትምህርት ለማስቀጠል መምህራን ተማሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁና የመተላለፈያ መንገዶችን እንዲሁም ጥንቃቄዎችን በማስተማር ተማሪዎች እንዲተገብሩት ከማድረግ አኳያ ከመምህራን ፋና ወጊ ስራ እንደሚጠበቅ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር በመክፈቻ ንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡

 

በአውደጥናቱ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ደረጃ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ  ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ መምህራን ዜጎችን በስነምግባርና በእውቀት ቀርፆ መልካም ዜጋ ከማፍራት አንፃር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ሁሉ የትምህርት ስርዓቱን ማየትና በአግባቡ መፈተሸ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ የአንድ ሀገር እድገትና የዜጎቿን ስነ-ምግባር ለመገንባት ቅድሚያ የመምህራንን አቅም የሚያጎለብቱ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ብቁ እንዲሆኑ ማድረግና በተለያየ መልኩ ከመምህራን ማህበር ጋር በጋራ መስራትና የመምህራን አቅም የበለጠ ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ  ዶ/ር ሙሉነሽ ገልጸዋል። አያይዘውም ከሙያው አንፃር ሲታይ መምህራን ተገቢውን ጥቅምና ክብር አለማግኘታቸው ቢታወቅም  የመምህርነት ሙያ ክብር በሚከፈላቸው ደሞዝና ባላቸው የኑሮ ደረጃ መታየት እንደሌለበት ጠቁመው ለመምህራን የሚገባቸውን ክብርና እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተናግረዋል። 

 

በአውደጥናቱ  “የአለም የመምህራን ቀን አከባበር ታሪካዊ አመጣጥና በሀገራችን የመከበሩ ዳራው“፤ በዶ/ር ዮሐንስ በንቲ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት፣የመምህራን ትምህርት ስልጠናና ስምሪት ታሪካዊ ጉዞ በኢትዮጵያ፤ በፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ እና በአቶ ደረጀ ታዬ፣ የትምህርት ሙያ በባለሙያውና በማህበረሰቡ ያሉት እይታዎችና የገፅታ ግንባታ አስፈላጊነት፤ በፕሮፌሰር አለማየሁ ቢሻውና በዶ/ር ታደሰ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ሙያዊነት፤ በዶ/ር ዳዊት አስራት እና በዶ/ር አንዳርጋቸው፣ የትምህርት ስራ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ቀውሶች ወቅት በፕሮፌሰር ረዳ ዳርጌና በዶ/ር አስናቀ ታረቀኝ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መካከል ሆኖ ማስተማርና የትምህርት ስራን የመምራት ወቅታዊ ጥሪ ትኩረቶች በዶ/ር ይልቃል ከፍአለ የአማራ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበው በዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል፡፡

 

በምክክር መድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ ወ/ሮ እምየ ቢተውን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣  እንዲሁም የመምህራን ማህበር ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

በመጨረሻም አቶ በቀለ መንገሻ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ጉዳይ ኃላፊ እና ወ/ሮ እምየ ቢተው በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ የምክክር መድረኩን በንግግር ዘግተውታል፡፡