እንቦጭን በዘመቻ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ  ለማጥፋት የተጀመረውን ሀገራዊ ዘመቻ ተቀላቀለ

 

በሙሉጌታ ዘለቀ

 

የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ለማስወገድ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ የቆየው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ዘመቻ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሩ ቦታው ድረስ በመሄድ አስጀመረ፡፡ 

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሐይቁ ላይ የእንቦጭ አረም  መከሰቱን ለባለድርሻ አካላት ከማሳወቅ ጀምሮ አረሙን ከሐይቁ ለማጥፋት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጠንካራ ስራዎችን መስራቱን ጠቅሰው ለዚህም የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት  የመካኒካል ምህንድስና መምህራን ዲዛይን በመስራትና የሙላት ኢንጂኒየሪንግ የእንቦጭ መሰብሰቢያ ማሽን ማምረቱን አስታውሰው ላደረጉት መልካም አስተዋፃ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡  ዶ/ር ፍሬው አክለውም ከዘመቻው ባሻገር ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የእምቦጭ አረም በዘላቂነት እንዲወገድ ከተፈለገ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ከዘመቻ ባለፈ በቋሚነት በመናበብ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው  የእንቦጭ አረምን ከሀይቁ ለማስወገድ በዘመቻ የሚሰሩ ስራዎች ውጤት እንደማያመጡ በመገንዘብ በቋሚነት በርካታ የሰው ሀይልን እና  ማሽኖችን በመጠቀም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሰው ሃይል አረሙን በማስወገድ ሂደት ለሚያጋጥሙ ማንኛውም ጉዳቶች  በቦታው ሀኪሞችን በመመደብና  ቋሚ የማረፊያ ቤቶች እንዲሰሩ  ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ቦታው ድረስ በመገኘት በጉዳዩ ላይ  መምከሩን ተናግረዋል፡፡

 

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም የእንቦጭ አረም የሀይቁን 4300 ሄክታር የሽፈነ ሲሆን አረሙን የማስወገድ ዘመቻው ሽሃ ጎመንጌ ቀበሌ መጀመሩን ጠቅሰው አፈፃፀሙ እየታዬ ስራው በአስሩም ቀበሌዎች እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡

 

አረሙን የማስወገጃ ቦታዎችን በመምረጥ በማከማቸት አድርቆ ለገበሬው ማሳ ኦርጋኒክ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ምርምር እየተደረገበት መሆኑን በዘመቻው ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡