ስልጠና

                    ተማሪዎችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስልጠናው እንደቀጠለ ነው

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዳይሬክቶሬት በ2013 ዓ/ም የተማሪዎችን ቅበላ ምክንያት በማድረግ በተላያዩ ክፍሎች ለሚሰሩ የተማሪዎች አገልግሎት ሰጭ የአስተዳደር ሰራተኞች የጀመረውን ስልጠና አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወርቁ አበበ በስልጠናው ዙሪያ በሰጡት ገለፃ በሁሉም ግቢ ለሚገኙ የምግብ ቤት አስተናጋጆች ስለደንበኞች አገልግሎት፣ በዋናዉ ግቢና ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ለሚገኙ ለጸጥታና ደህንነት ሰራተኞች በደንበኞች አገልግሎትና ጥበቃ፣ በሁሉም ግቢ ለሚገኙ ፕሮክተሮችና የጽዳት ሰራተኞች በወቅታዊው  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ዓለምአቀፋዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ፣ ስለ መተላለፊያ መንገዶችና መወሰድ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ተገቢ የሆኑ ባለሙያዎችን በማስመጣት ስልጠና እየሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ ወርቁ እንዳሉትም ሰራተኞቹ በስልጠናው የሚያገኙትን እውቀት ካላቸው ሰፊ ልምድ ጋር በማስተጋበር ተማሪዎች በሚመጡበት ወቅት እንደ ልጆቻቸው ወይም እንደ ቤተሰብ አባላቸው እንዲያስተናግዷቸው አደራ ብለዋል፡፡

በስልጠናው ያገኘናቸው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከስልጠናዉ ከፍተኛ የሆነ ዕዉቀትና ግንዛቤ በማግኘታቸዉ መደሰታቸዉን በመግለጽ በሰለጠኑበት አግባብ ደንበኞቻቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ከ1087 የማያንሱ በተለያየ ዘርፍ የሚሰሩ የአስተዳደር ሰራተኞች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡