ዝክረ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩሊቲ ለፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የመታሰቢያ መርሀ ግብር አካሄደ፡፡

በትዕግስት ዳዊት

በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በተለይም በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ፣ በሀገራችን ፖለቲካ እና በርከት ያሉ ተግባራትን በመከወን ዘመን የማይሽረው አስተዋጽ አበርክተው እና አሻራ ትተው ያለፉትን ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን በጥቂቱ ለመዘከር የተደረገ መርሀ ግብር መሆኑን መርሀ ግብሩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ  ተናግረዋል፡፡

 

ደ/ር ቃለወንጌል አክለውም ወደፊት የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን ጨምሮ የሌሎችንም በተለያየ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ለሆኑ የአንጋፋ ምሁራን ስራዎች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ መርሀ ግብሮች፣ እንዲሁም ውይይቶችን በሰፊው እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

በማስከተል የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም አጭር የህይወት ታሪክ በዶ/ር አረጋ ባዘዘው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ቀርቧል፡፡

የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የቀድሞ ተማሪ የነበሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ፈረደ ዘውዱ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የአስተማሪነት ዘመን ትዝታቸውን ያካፈሉ ሲሆን ፕሮፌሰሩን ሀገር ወዳድ፣ ለወገን ተቆርቋሪና ጀግና ምሁር ሲሉ አውስተዋቸዋል፡፡

በተጨማሪም ዶ/ር ጥጋብ በዜ እና ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በህይወት ዘመናቸው ስላበረከቷቸው ታሪክዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበረሰባዊ ይዘት ስላላቸው መጽሀፍት፣ ስላዘጋጇቸው የማስተማሪያ መጻህፍት እንዲሁም ስለ ማህበራዊ ህይወታቸው የሚዳስስ ወረቀት አቅርበዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ዘመን ተሸጋሪው የአደባባይ ምሁርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች መሆናቸውም ተወስቷል፡፡

በመርሀ ግብሩ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የቀድሞ ተማሪዎች፣ የስራ ባልደረቦች፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ታድመዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ መክፈቻ የሻማ ማብራት ስነ-ስርአት እንዲሁም የሁለት ደቂቃ የህሊና ጸሎት በሊቀ-ህሩያን በላይ መኮኘን የተደረገ ሲሆን በመጨረሻም የደራሲያን ማህበር ባህር ዳር ቅርንጫፍ ፕሬዚዳት የሆኑት ሊቀ-ህሩያን በላይ መኮንን የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን ህልፈት አስመልክተው አጠር ያለ ግጥም አቅርበዋል፡፡