የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ውይይት

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ውይይት ተካሄደ ፡፡

የአገሪቱን የአሳ ግብርና ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ለማስጀመር Advancing Climate Smart Aquaculture Technologies (ACliSAT) በሚል ርዕስ ከመስከረም 22-23 አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡ በአውደ ጥናቱ  በዋነኛነት የፕሮጀክቱን ትግበራ ማስጀመር በሚቻልባቸው፣ በትብብር መስራት በሚያስፈልግባቸው ጉዳዮችና በአጠቃላይ የአገሪቱን የአሳ ግብርና ማሳድግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው፣ ሰፊና ገንቢ ውይይት ተደርጓል፡፡  

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋየ ሽፈራው  ዩኒቨርሲቲው ዘንዘልማ በሚገኝው ካምፓሱ ከቅድመ ምረቃ እስከ ፒኤችዲ ደረጃዎች በአሳ ልማት ዘርፍ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋየ አክለውም ጣና ሀይቅ አካባቢ የአሳ ሀብታችንን በተሻለ መንገድ ለመጠበቅ የሞዴል ፋርም ተገንብቶ ለስልጠና እና የአሳ እርባታን ለማዘመን እየተሰራ ቢሆንም በሃገሪቱ ፈጣን የህዝብ ብዛት፣ ከፍተኛ የወጣት ሥራ አጥነት መጨመር እና ከተጋረጠብን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ሲነፃፀር ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በላይ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዋሴ አንተነህ በበኩላቸው የእለቱ አውደ ጥናት ዋና አላማ የአሳ ግብርናን በኢትዮጰያ ማስፋፋት በሚቻልበት ዙሪያ በIFAD እና WorldFish ድጋፍ የሚተገበረውን ፕሮጀክት በማስጀመር ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ 

ዶ/ር ዋሴ ፕሮጀክቱ ኤርትራና ግብፅን እንደሚያካት ጠቁመው፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በኢትዮጵያ ያለውን የውሃ ልማት በተመለከተ ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲያስፈፅም ተወከሎ እያስተባበረ ይገኛል ብለዋል፡፡