መጽሐፍ ተመረቀ

የባሕር ዳር ከተማን አመሰራረትና የነዋሪዎቿን ታሪክ የሚዘክርና የዩኒቨርሲቲያችን ባልደረባ በነበሩት በአቶ ያረጋል ገረመው የተፃፈ መጽሐፍ ተመረቀ፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅረሰላም ጋረድ ለስነሥርዓቱ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት የባሕር ዳር ከተማን ታሪክ እንዲህ በተደራጀ ሁኔታ ጽፎ ለአንቢያን ማድረስ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአቶ ያረጋል የተበረከተው ‹አቦካቦት› የተሰኘ መጽሐፍ የከተማዋን የቀደመ ታሪክ በጥልቀት የሚያትትና የባሕር ዳር ከተማንና የነዋሪዎችን ታሪክ ለትውልድ የማስተላለፊያ መንገድ እንደሚሆን እንዲሁም ለታሪክ ተመራማሪዎች በማጣቀሻነት እንደሚያግዝ አበክረው ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ፍቅረሰላም በተጨማሪም ለወደፊት በዚህ ስራ እንደማያቆሙና ከዚህ በበለጠ የባሕር ዳር ከተማን እና የነዋሪዎችን ታሪክ በሌላ መጽሐፍ ይዘው እንደሚመጡ ያላቸውን እምነት አስተላልፈዋል፡፡

መጽሐፉ የባሕር ዳር ከተማ ከዛሬ አንድ መቶ አመት በፊት አንድ በጣም ትንሽ መንደር ሆና ጥቂት በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይኖሩባት የነበረች ትንሽ መንደር ከነበረችበት አንስቶ አሁን እስከደረሰችበት ደረጃ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈች ያስነብበናል፡፡

ባሕር ዳር ታሪኳን በጽሑፍ የሚያሰፍሩ የውጭ አገር ዜጎች እና የሀገር ውስጥ የታሪክ ምሁራን ከከተሙባት ጊዜ ጀምሮ የክልል ርዕሰ ከተማ እስከሆነችበት ጊዜ ድረስ በርካታ የአመራር አካላት በታሪክ ቅብብሎሽና የሥራ ተነሳሽነት እንዳስተዳደሯት ያነሳል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዋና ፀሀፊ የሆኑት ፕሮፌሰር አብይ ይግዛው ስለ መጽሐፉ አጠቃላይ አስተየት ሰጥተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አብይ በገለጻቸው ‹አቦካቦት› በቋንቋ አጠቃቀምና በአጠቃላይ በጽሑፉ ይዘት የተዋጣለት ስራ ከመሆኑም በላይ ስለ ባሕር ዳር ታሪክ ምሉዕ የሆነ ጽሑፍ ይዞ የቀረበ የመጀመሪው ጽሑፍ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ በየዘመኑ የነበሩት ነዋሪዎቿን ከፍተኛ ጥረት አድርገው አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ስላደረሷት ታሪክ የማይዘነጋቸው ጥሩ ተምሳሌትና ፈርጦች ሲሉ አሞካሽተዋል፡፡

ረዥሙና ጠመዝማዛው የዓባይ ወንዝ፣ በሩቅ ተንጣሎ ሲያዩት ቀልብን የሚማርከው የጣና ሐይቅ እና የቀደመውን ዘመን ታሪክ በውስጣቸው የያዙት የጣና ገዳማት ለጎብኝዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መስህቤች መሆናቸውን አቶ ያረጋል በመጽሐፋቸው አሳይተዋል፡፡

መጽሐፉን የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ተወካይና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን አየሁ እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅረሰላም ጋረድ በጋራ መርቀውታል፡