የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል አንደኛውን አገር አቀፍ ጉባኤ አካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል አንደኛውን አገር አቀፍ ጉባኤ ከሰኔ 2-3 በዋናው ግቢ አዳራሽ አካሄደ፡፡

የኮንፈረንሱ አጀንዳ በርከታ ያሉ አንገብጋቢ የማህበረሰብ ጉዳዮችን የሚዳስስ መሆኑንና በተለይ የስደተኞችን አኗኗር፣ ህገወጥ ስደት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የቱሪዝም ልማት፣ ማህበረሰቡን ያማከሉ ድርጅቶች በልማታዊና በሥራ ላይ ያላቸውን ሚና፣ ወቅታዊ የሆኑ ማህበራዊ ችግሮች፣ የከተሞች አመሰራረትና ተያያዥ ጉዳዮች፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ጥቅም ላይ የሚውሉ አገር በቀል ስልቶች እንዲሁም ልማትና የመሳሰሉ ወሳኝ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት እንደሚሆን የገለፁት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የማሕበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ምክትል ዲን የሆኑት ዶ/ር ሳምሶን ጫኔ ናቸው፡፡

የማህበረሰብ (የአንቶሮፖሎጂ) የትምህርት መስክ በጊዜ ቀመር ውስጥ የሰው ልጆች ያላቸውን የባህል ተመሳስሎና ልዩነት የሚያጠና የሚተነትንና እውቀት የሚያስጨብጥ የንጽጽር ሳይንስ እንደሆነና ከእውቀትና ክህሎት አመንጭነቱ ባሻገር በክልሉ የሚገኘውን ህብረተሰብ የባህል ተመሳስሎና ልዩነት በማጥናት የሚያመሳስሉ ነገሮች ይበልጥ የሚጠናከርበት፣ የሚያለያዩን የባህል እሴቶች ደግሞ አውቆ በማክበር ሰላማዊ ህይወት የምንቀጥልበትን መንገድና ዘዴ በማሳየትና በመጠቆም በተግባር ምርመራ መተርጎም የሚያስችል ዘርፍ እንደሆነና በተለይ አሁን የምንገኝበት ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ከልዩነቱ ጋር በሰላምና በአብሮነት መንፈስ፣ ተቻችሎና ተሳስቦ የመኖር ሁኔታ በልዩ ልዩ አለም አቀፍና ሀገራዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ከፍተኛ አደጋ የተደቀነበት ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ የዘርፉን ጥናትና ትንታኔ ከመቼውም በላይ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሚያደርገው የየተናገሩት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሂሩት ካሳው ናቸው፡፡

የቢሮ ኃላፊዋ አክለውም ያለፈው ትውልድ ትሩፋት ባህሉ የሆኑ የራሱ በሚላቸው ወግና ልማዶቹ በመመስረት እያሰበ፣ እየፈጠረ፣ በዚህም እየተመራ፣ እየተዳደረ፣ ባህላዊ ማንነቷና መሰረቷ የተጠበቀ ሀገር አሁን ላለው ትውልድ ማስረከብ እንደቻለና የአሁኑ ትውልድም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ተግባራትን ተቀናጅተን በከፍተኛ ርብርብና ፍጥነት ማከናወን ከመቼውም ጊዜ በላይ የመጠበቅ ጉዳይ እንደሆነ እና ከዚህ አንፃር ገና ያልተነካው የክልሉ ማህበረሰብ የአስተሳሰብ ውጤት የሆነውን ባህልና ወግ በተገቢው በመፈተሽና በማጥናት በአግባቡ ተመዝግቦና ተሰንጾ እንዲገኝና ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ፣ የማህበረሰቡ ልዩ ልዩ ባህልና ወጎች በተገቢው እንዲታወቁና እንዲጠበቁ ለማስቻል፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ የብዙኃን መገናኛዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑበትን ስልት የመቀየስ፣ እንዲሁም የተለያዩ የማስተማሪያና የግንዛቤ ማስጨበጫ አማሪጮችን በመጠቀም ማህበረሰቡ በዚህ ዘርፍ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ቀስ በቀስ ለማጥበብ የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት የዚህ ትምህርት ክፍል ዋነኛ የሥራ ድርሻ መሆኑም መዘንጋት እንደሌለበትና በዚህ ረገድ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የክልሉን ባህል በለውጥ ጎዳና ለመምራትና ሀገሪቱ ካወጣቻቸው የዕድገትና የትንስፎርሜሽን የልማት ዕቅድ ጋር የሚጣጣም ባህላዊ ስርዓት ለመገንባት የበኩሉን ያለሰለሰ ሥራ እያከናወነ እንደሆነ እና የሶሻል አንትሮፖሎጂ የትምህርት መስክ በሚያደርገው ማነኛውም የማህበረሰብ ባህል ጥናትና ልማት እንቅስቃሴ ከጎኑ በመሆን በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ የቢሮ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡ 

ይህ ጉባኤ ሶስት ዋና ዓላማዎችን በማካተት ማለትም ስለ ትምህርት ክፍሉ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመገናኘት ለወደፊት እንዴት መስራት እንዳለባቸው ለመመካከርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2017 ዓ.ም አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አስር ግንባር ቀደም የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ለመሆን ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ በመሆኑ ይህ ራዕይ ይሳካ ዘንድ የትምህርት ክፍሉ የራሱን ድርሻ ለመወጣት የተለያዩ ምርምሮችን ለማካሄድ የበለጠ ልምድ ለመቅሰም ያግዛቸው ዘንድ የተዘጋጀ እንደሆነ የገለፁት የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ጉባይ አሳዬ ናቸው፡፡

ኃላፊው አክለውም የአንትሮፖሎጂ ትምህርት መስክ በሁለገብ መልኩ የሰው ልጆችን ባህል፣ ሃይማኖት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ከአካባቢው ጋር ያለውን እና የሚደረገውን መስተጋብር በማጥናት በማህበረሰቡ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡