የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ

የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ ርክክብ ተካሄደ
********************************************
በሙሉጐጃም አንዱዓለም
ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለባህር ዳር ከተማ ትምህርትና ጤና መምሪያ “Frances G. Cosco Foundation (FGCF)” /ኤፍ. ጂ. ሲ. ኤፍ./ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ በጐ አድራጐት ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ርክክብ ተካሄደ።

የመርሐ-ግብሩን መጀመር ይፋ ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕ/ር የሺጌታ ገላው ለታዳሚዎች የእንኴን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡አክለውም ወቅቱ ሀገራችንን ጨምሮ ሁሉም የዓለም ህዝብ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ፍልሚያ የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመው ለተደረገው ድጋፍ በኮሌጁ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ድርጅቱ ከአሁን በፊት ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ለሌሎች ተቋማት በርካታ ድጋፍ እንዳደረገና ድጋፉ ወረርሽኙ ከሚጠበቀው በላይ በጨመረበት ወቅት መሆኑ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አውስተው በሆስፒታሉ ስም ቢሰጥም ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ አገልግሎት እንዳለው በመግለፅ ለወደፊት ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋና አቅርበው ድርጅቱ ከአሁን በፊት “ትምህርት ለለውጥ” በሚል መሪ ቃል ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር አራት ትምህርት ቤቶችን ከተለመደው ወጣ ባለ እና በተሻለ መንገድ እንዲገነባ በማድረግ በርካቶ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተጨማሪም ሆስፒታሉ መማር ማስተማርን ምርምርን እና የማህበረሰብ አገልግሎትን ሶስቱንም የዩኒቨርስቲውን አምዶች አሳልጦ እየሰራ መሆኑን ም/ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የበጐ አድራጐት ድርጅቱ የአማራ ክልል አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብዮት አሸናፊ ድርጅቱ በአማራ ክልል በተመረጡ 5 ዞኖች እንደሚሰራና ለወደፊትም ተደራሽነቱን እንደሚያስፋፋ ገልፀው ከዩኒቨርሲቲው ጋርም በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።

አስተባባሪው በማከልም የቀረቡት ቁሳቁሶች 11 አይነት እንደሆኑና ለዩኒቨርሲቲው፣ ለባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ እና ጤና መምሪያ ጭምር በገንዘብ ቢተመን ከ6 መቶ ሺህ ብር በላይ ድጋፍ እንዳደረጉ ተናግረው በክልሉ ለሚገኙ ለ14 ትምህርት ቤቶችም 4 ሰዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስታጥብ ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ከቁሳቁሶች መካከል ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ባለሙያዎች አልባሳትና ከንክኪ ነፃ የሆነ የሙቀት መለኪያ እንደሚገኙበት አስገንዝበው ለወደፊት ት/ት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ት/ቤቶች ቢከፈቱ ተማሪዎችን በምን ዓይነት መልኩ ከወረርሽኙ መታደግ እንደሚገባ እንዲሁም የዓይን ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለማገዝ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ አስተባባሪው ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሻገር አዳሙ ድርጅቱ በተለይ ትምህርት ላይ መሬት የነካ ስራ በስፋት እየሰራ መሆኑንና 5 ትምህርት ቤቶችን በፍጥነትና በጥራት አስገንብቶ ምቹ ክፍሎችን በመፍጠር አኩሪ ተግባር እንዳከናወነ ተናግረው አሁን ለተደረገው ድጋፍም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ተስፋ ሞላ በአሁኑ ወቅት በሃገራችንም ሆነ በከተማችን ወረርሽኙ እየተስፋፋ ባለበትና የመከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት በተከሰተበት ወቅት እርዳታው መድረሱ አስፈላጊ ጊዜ ላይ እንደሆነ አስገንዝበው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ርክክቡ የተካሄደው በድርጅቱ አስተባባሪ አቶ አብዮት እና በዶ/ር ተስፋዬ አማካኝነት ሲሆን የጥበበ ጊዮንን ፕ/ር የሺጌታ፣ የባህር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያን አቶ ተሻገር እና የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያን አቶ ተስፋ ተረክበዋል።