የጉና-ጣና ተፋሰስ ችግኝ ተከላ

 

 “የተባበረ ክንድ ጣናን ለመታደግ”

ሰኔ 19/2012 ዓ.ም

በሙሉጌታ ዘለቀ

------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

"ጣናን ለመታደግ የጋራ፣ የትብብርና የፍቅር አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ወደ ጉና" በሚል መሪ መልዕክት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የደብረታቦር፣ የደባርቅ፣ የጎንደር፣ የእንጅባራ እና የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች የጉና-ጣና ተፋሰስ ቦታዎች ላይ ችግኝ ተክለዋል፡፡

 

የችግኝ ተከላውን ሲያከውኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከጉና ተራራ የሚነሱ ወንዞችና መጋቢ ጅረቶች ተከዜንና ጣናን የሚሞሉ መሆናቸው እና ጉና ተራራን በደን መሸፈን የተፈጥሮ ሃብቶችን ለመጠበቅ ዋስትና መሆኑን መነሻ ያደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በእለቱም የጉና ተራራ ጣና ተፋሰስ አካባቢን ለማልማት የተደረገ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓትም ተካሂዷል፡፡

 

በዚህ ታሪካዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ አባይና ጣናን ለማዳን በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቅሰው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በከፍተኛ የተፋሰስ ቦታዎች ላይ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንና የጉና ተራራ አካባቢ ተኮር የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ምርምሮች እየተሰሩ መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

 

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ፣ ከመጤ አረሞች እንዲሁም ከደለል ለመታደግ ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል ከመሆን ይልቅ በጋራ ሁነው የምርምር ስራዎችን መስራታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የጉና አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን መስራት ብሎም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አካባቢውን የጋራ የምርምር ማዕከል ማድረግ ጊዜው የሚፈልገው መሆኑን ተናግረው የዕለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የእንቅስቃሴው መነሻ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

 

 

በተጨማሪም በክምር ድንጋይ ከተማ በሚገኘውና በመከላከያ በተገነባው የደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ ምዕራብ እዝ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግኝ ተከላ ተከናውኗል፡፡ 

 

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የተጀመረው የስድስቱ ዩኒቨርስቲዎች የጉና ተራራ አከባቢን የማልማት የችግኝ ተከላ መረሀ ግብር የመጨረሻ መዳረሻውን ጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር በማድረግ ጉብኝት አካሂዷል፡፡

በዚህ ታሪካዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የስድስቱም ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የዞን አስተዳዳሪዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡