የከፍተኛ አመራሮች ግብረ-ሀይል ምክክር

ከፌደራል እና ከክልል የተውጣጡ የከፍተኛ አመራሮች ግብረ-ሀይል ታህሳስ 17/ 2012 ዓ.ም. ከባህር ዳር ከተማ የሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ከወጣቶች እና ከክፍለ ከተማ ተወካዮች ጋር በመማር ማስተማሩ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ምክክር አደረጉ፡፡
=======================================================
በሙሉጌታ ዘለቀ
በተለያዩ ጊዜያት በዩኒቨርስቲዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከተማሪዎች እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን ። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ከታህሳስ 13 ጀምሮ ከተማሪዎች፣ከዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል። ዛሬም ከባህር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከከተማው ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።
 
ውይይቱን ግብረ-ሀይሉ ወደ ዩኒቨርሲቲው ይዞት የመጣውን ዋና ተልዕኮ በመናገር የመጀመሩት አቶ አማረ አለሙ የባህር ዳር ከተማ ም/ከንቲባና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ም/ሰብሳቢ ናቸው፡፡ አቶ አማረ እንዳሉት የባህር ዳር ከተማ ማህበረሰብ በተለያዩ አደረጃጀቶች በመሆን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከቅበላ ጀምሮ ሰላምን በማስጠበቅ ቀላል የማይባል አሰተዋፆ ማበርከታቸውን ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና የአካባቢው ህብረተሰብ ያላቸውን ሁለንተናዊ ቁርኝት ጠቅሰው፤ አሁን እንደ ሀገር ያጋጠመንን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላም እጦት ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን መስራትና ቀደም ሲል የነበረውን ሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ወደ ቦታው መመለስ ይገባል ብለዋል፤ ለውጤታማነቱም ይህን መሰል ውይይት ማድረጋቸው ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
በውይይቱም ላይ ህብረተሰቡ የዩኒቨርሲቲው ሰላም መሆን የከተማዋም ሰላም መሆኑን ገልፀው የዩኒቨርሲቲው ሰላም ሲታወክ የከተመዋም ገፅታም እንደሚደበዝዝ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ከአስር ሺህ በላይ ሰራተኞችና ከሃምሳ አራት ሺህ በላይ ተማሪዎችን የያዘ ግዙፍ ተቋም በመሆኑና በአንድም በሌላ ለከተማው ማህበረሰብ የኑሯቸው መሰረትም ስለሆነ ለሰላሙ መጠበቅ አጥብቀው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችም በሚከሰቱ ወቅታዊ ችግሮች ሳይበገሩ ትምህርታቸውን መማር እንዳለባቸው እና ማንኛውም የባህር ዳር ከተማ ህብረተሰብ በሰላሙ ዙሪያ ከጎናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተማሪዎች መካከል ተማሪ መስለው በብሄርና በቋንቋ ግጭትን ለመፍጠር ወረቀት የሚበትኑት አካላት ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ከፅጥታ አካላትና ከከተማው ህብረተሰብ ውጭ ሰላልሆኑ ተይዘው ለህግ እንዲቀርቡና በግጭቱ ምክንያት ግቢውን ለቀው የወጡ ተማሪዎችንም በሚዲያ እንዲጠሩና እንደገና ምዝገባ ተካሂዶ ትምህርታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ተሰብሳቢዎች ሀሳባቸውን ተናግረዋል፡፡ ካሁን በፊት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ “ባህር ዳር እንደቤቴ ” በሚል የተጀመረው እና በአሁኑ ሰዓት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በስፋት የተገበረውና ውጤታማ የሆነበት ከአማራ ክልል ውጭ የመጡ ተማሪዎችን ህብረተሰቡ እንደ ልጁ አድርጎ የሚንከባከብበት ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ተማሪዎች በታላላቅ በዓላት ከባህር ዳር ነዋሪዎች ጋር ሲያከብሩ መቆየታቸውን አስታውሰው በዚህም ብቸኝነት ሳይሰማቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር የሆኑ ያህል እንዲሰማቸው ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ በጎ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጋራ ሀሳብ የተያዘ ሲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎችም የበኩላቸውን ለማድረግ ቃል ገብተዋል ፡፡
 
የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሃጂ ኢብሳ እንዳሉት ከአመታት በፊት ወደ ተማሩበት ዩኒቨርሲቲ በድጋሚ ስለመጡ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው ህብረተሰቡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ግጭቶች ሲከሰቱ በየኔነት ስሜት ከፀጥታ ሀይሉ እና ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን ተማሪዎችን በመምከርና በመገሰፅ የሰላም አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አቶ ሃጂ ቀጥለውም አሁን በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እና ክልሎች እየታዩ ያሉት ጎሳን መሰረት ያደረጉ የሚመስሉት ግጭቶች ሰፊውን የኦሮሞን እና የአማራን ህዝብ ፈፅሞ እንደማይወክል ገልፀዋል፡፡ይልቁንም ጉዳዩ ላለፉት ሶስት አስርት አመታት የተጠነሰሰ ሴራ ውጤት መሆኑን ጠቁመው የባህር ዳር ከተማ ህብረተሰብ ሴራውን እንደ ከዚህ ቀደሙ በተባበረ ክንድ እንዲያከሽፈው ጥሪ አድርገዋል፡፡
 
በእለቱ መድረኩ ላይ የነበሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኜ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት የኖረው በሀገር ሽማግሌዎች፣ በጸጥታ አካሉ እና በህብረተሰቡ ትልቅ እገዛ መሆኑን ጠቅሰው ላበረከቱት አስተዋፆ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም ስለፖሊ ተማሪዎች መውጣት ከህብረተሰቡ ለቀረበው ጥያቄ ሲያብራሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸውን የክልል ባለስልጣናት እና የሀገር ሽማግሌዎችን በመያዝም ውይይቶች እንደተደረጉ አንስተው ነገር ግን ተማሪዎች ትምህርት ሳይማሩ ለበርካታ ሳምንታት መቀለብ ስለማይቻልና ህጉም ስለማይፈቅድ ከብዙ ጥረት በኋላ ከአቅም በላይ ስለሆኑ ከግቢ መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ዶ/ር ፍሬው ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኙት ሁሉም ተማሪዎች ህጋዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙት መማር ሲችሉ ብቻ መሆኑን ተናግረው የወጡ ተማሪዎችን ለመመለስና በተጠናከረ መልኩ ትምህርት ለማስጀመር የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ገልፀዋል፡፡