የነጭ ሪቫን እና የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን ተከበረ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክተር እና የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት የነጭ ሪቫን እና የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን በደመቀ ሁኔታ አከበሩ፡፡

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣መምህራን እና የአስተዳደር ሰራኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የነጭ ሪቫን እና የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን ተከብሯል፡፡ በእለቱም ኤች አይ ቪ ኤድስን ከሚመለከቱት ጉዳዮች ባሻገር የሴቶች ትንኮሳና ጥቃትን ያካተቱ የተለያዩ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው ደመቀ ውይይት  ቀኑ ተከብሮ ውሏል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ሲስተር ኤደን አምሳሉ እንዳሉት መድረኩ በሀገራችን በፖለቲካው ትኩሳት ምክንያት የግንዛቤ ፈጠራ ስራው እየተቀዛቀዘ የመጣውና ለሀገራችን ትልቅ ስጋት እየፈጠረ ያለውን የኤች አይ ቪ ኤድስ እንዲሁም የሴቶች ጥቃትና ትንኮሳን ለመቀነስ ብሎም ለመግታት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊዋ አክለውም ያለወንዶች እገዛ ጥቃትንም ሆነ ትንኮሳን መቀነስም ሆነ መቆጣጠር አይቻልም ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ብርሃኔ መንግስቴ እንዳሉት ክፍሉ ከማህበራዊ ጤናና ልማት ድርጅት ጋር በመሆን የነጭ ሪቫን ቀንን በአለማቀፍ ደረጃ ለሃያ ስምንተኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ እንዲሁም በክልላችን ለ10ኛ ጊዜ "Orange the world: Generation Equality Stands Against Rape" በሚል ርዕስ እንዲሁም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ31ኛ ጊዜ "ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፆታዊ ትንኮሳና ጥቃት በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚፈፀም ተግባር ቢሆነም በተለይ የችግሩ ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሯ አክለውም የነጭ ሪቫን ቀንን ስናከብር በወንዶች አጋርነትና ተሳትፎ በሴቶች የሚደርሱ ጥቃቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ግንዛቤ መፍጠርን ያለመ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይም እለቱን በማስመልከት ወቅታዊ የኤች አይ ቪ ስርጭትና የመቆጣጠር ሂደቱን በተመለከት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እና በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ያለውን የቫይረሱ ስርጭት በሙሁራን ጥናታዊ ፁሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ግቢዎች የመጡ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ባለው የኤች አይ ቪ ስርጭት እና በሴት ልጅ ትንኮሳና ጥቃት እንዲሁም በግቢው ውስጥ ባለው የኮንዶም ስርጭት ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የኮንዶም ስርጭቱ ተማሪዎች ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነትን እንዲፈፅሙ የሚገፋፋ እንዳይሆን ስጋታቸውን ገልፀው ከጎን ይህንን የሚገታ የተለያዩ መልዕክቶች የሚቀመጥበት መንገድ መኖር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከተማሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎች ሲስተር ኤደን አምሳሉ እና የጥናታዊ ፁሁፎች አቅራቢዎች አቶ ተናኘ ይስማውና አቶ ባዬ አበራ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም የይባብ ግቢ የኤች አይ ቪ ክበብ አባላት ተማሪዎች እለቱን በተመለከተ ታዳሚውን እያዝናና ቁምነገር የሚያስጨብጥ ጭውውት አቅርበዋል፡፡

Date: 
Thursday 17, 2019
place: 
Bahir Dar University
December, 2019