Latest News

ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ እውነታውና አቅጣጫው

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋክልቲ አዘጋጅነት ‹‹ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ እውነታውና አቅጣጫው››  በሚል ርዕስ ተጋባዥ ምሁራን በተገኙበት በዩንቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት ተካሄደ ፡፡

የመወያያ ፅሁፉ በታዋቂው ምሁር ዶ/ር ታየ ብርሃኑ የቀረበ ሲሆን በዋነኛነትም አቅራቢው በኢትዮጵያ የፌደራልዝም አመሰራረትና አተገባበር፣ የፌደራሊዝም ምስረታ መነሻ ሀሳብ ምንነትና አደረጃጀት የሚሉ ሀሳቦች ላይ ተኩረት ያደረገ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ታየ በፅሁፋቸውም ስለ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሲናገሩ በጎሳ ላይ መሰራት ያደረገ መሆኑ በአለማችን ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቷን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ ስለመሆኑ ጥየቄን እንደሚያጭር ገልፀዋል፡፡

ፅሁፍ አቅራቢው አክለውም ሶስቱን የመንግስት ቅርሶች አሃዳዊ፣ ፌደራላዊና ኮንፌዴሪሽን የሚሉትን በመተንተን በኢትዮጵያ እና በሌሎች አገሮች የፌደራሊዝም ባህሪያትና ገፅታ በንፅፅር አቅርበዋል፡፡ በዚህም ከታዳሚው የግልፅነት ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግቢዎች የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የጽዳት ስራ ምክኒያት በማድረግ ሚያዝያ 06/2011 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ግቢዎች የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ስራተኞችና ተማሪዎች የተሳተፉበት ይህ ዘመቻ ከየግቢው ቀላል የማይባል ደረቅ ቆሻሻን ከማስወገድ ባለፈ አብሮ የመስራት ባሕልን በማሳደግ ሌሎች የጋራ ርብርብ የሚፈልጉ ጉዳዩችን ሁሉ በትብብርና በጋራ በመስራት የተሻለ አካባቢን መፍጠር እንደሚቻል የታየበት ነው፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚኖሩ ወጣቶችና ሴቶችም የተሳተፉ ሲሆን በተለይም በኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ተሳትፎ ላደረጉት የአካባቢው ወጣቶች በተቋሙ ሃላፊዎች ምስጋናና የማስታወሻ ቲሸርት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ወጣቶቹ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ወደፊትም በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች አብረው መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ግቢዎች ማለትም በግብርና እና አካባቢ ሳይንስ፣ በህግና መሬት አስተዳደር፣ በዋናው ግቢ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በሌሎችም ክፍሎች የጽዳት ዘመቻ የተካሄደ ሲሆን በዋናው ግቢ በተለይም በሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና በጎልማሶች ትምህርት ክፍል (Adult Education) ተማሪዎችና ጥቂት መምህራን የተደረገው ግን ከሁሉም የጎላና በተምሳሌትነቱ የሚጠቀስ መሆኑን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ይህም የጽዳት ዘመቻ በየወሩ እንደሚካሄድ ከአስተባባሪዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡   

የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ 6ኛውን አገር አቀፍ ጉባኤ አካሄደ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ 6ኛ አመታዊ ትምህርታዊ ጉባኤውን  በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አካሄደ::

የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ ጥሪውን አክብረው ለመጡት ታዳሚዎች በሙሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን  አስተላልፈው ፋኩልቲው በ8 የቅድመ ምረቃ፣ በ11 የድህረ ምረቃ እና በ3 የሶስተኛ ዲግሪ (PhD) ፕሮግራም ከ5000 (አምስት ሺህ) ተማሪዎች በላይ ተቀብሎ  በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዲኑ አክለውም ፋኩልቲው ከሌሎች ኮሌጆችና ፋኩልቲዎች ቀድሞ የተቋቋመ ቢሆንም እስካሁን የሚጠበቅበትን ያህል መስራት እንዳልቻለ ጠቁመው የሰውን ልጅ በአግባቡ ለማነፅ ብሎም የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የማህበራዊ ሳይንስ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፤ በመሆኑም ፋኩልቲው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ በጉባኤው ከተለያዩ ተቋማትና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን የሚቀርቡት ጥናታዊ ፅሁፎችና ውይይት የማንቂያ ደወል ሆኖ እንደሚያገለግል እምነታቸው መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ስአት ፋኩልቲው የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችል በዕቅድና በተደራጀ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

መርሃ-ግብሩ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ዩኒቨርሲቲው በስምንት ግቢዎች በሶስቱም የስራ አምዶች ማለትም በመማር ማስተማሩ፣በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በመግለፅ ዩኒቨርሲቲውን በሰፊው እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ እንደማሳያም  ባህር ዳር ከተማን የትምህርት ከተማ ለማድረግ  በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በኩል ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው ተግባራት አመላካች እንደሆኑ ተናግረው የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲም ታሪክ ሳይዛባ ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ፖለቲካም በሳይንሳዊ ዘዴ ለማህበረሰቡ ማስተላለፍ ያለበትን መልዕክት እንዲያስተላልፍ እንዲሁም በጂኦግራፊውም ዘርፍ ብቁ ባለሙያ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ የሆነ አገራዊ ድርሻ እንዳለበት ተገንዝቦ በየአመቱ ጉባኤውን ማክበር ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ በመለየት ክፍተቶችን የሚሞላ ስራ ማከናወን እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የጉባኤውን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋብዘው የመጡት ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በውቀቱና የዩኒቨርሲቲያችን አንጋፋ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ ሲሆኑ ፕሮፌሰር ወልደአምላክ እንዳሉት የምርምር ስራዎች ተግባራዊነት አንዱ መለኪያ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆን ጥናት ማድረግ እንደሆነ ገልፀው ይህን እውን እስከምናደርግ ለውጥ የሚያመጣ ስራ እንዳልሰራን በማሰብ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ሲሉ ክፍተቱን ጠቁመዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በተለያዩ ሙህራን በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

5ኛው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ሳምንት አመታዊ አውደ ጥናት ተካሄደ
*****************************************************
የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት ‹‹ የባለ ድርሻ አካላት ሚና በቅርሶቻችን እንክብካቤ ›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 27, 2011 ዓ.ም. የግማሽ ቀን አውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡

በአውደ ጥናቱ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ኮሌጅ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አያሌው መለሰ በጥናታዊ ፅሁፋቸው እንዳቀረቡት ጣናን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ መጀመሪያ የሃይቁን ድንበር ማስከበር ይገባል ሲሉ፤ ለዚህም ምክንያቱ ጣና ከላይም ከታችም እሳት እየበላው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ከላይ የጣና ዳር ተራራ እየታረሰ መሆኑ፤ ከታች ደግሞ ወደ አባይና ጣና ሀይቅ የሚለቀቅ ቆሻሻ መኖሩ ምሆኑን ገልፀው ከዚህም ባሻገር ጣና በደለል በመሞላቱ ምክንያት እስከ ውሃው ዳር እየታረስ በመሆኑ 120 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የሀይቁ አካል በድን ሆኗል ብለዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከሚኒስተር መ/ቤቱ፣ ከባህር ዳር ከተማ ባህል ቱሪዝም እና ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የተጋበዙ መምህራንና ባለሙያዎች ተገኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡

ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የዩኒቨርሲቲው መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ ሴት መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች በተገኙበት መድረክ  በሴቶች በተለይም በዩኒቨርሲቲው ሴት  ተማሪዎች ተግዳሮቶች ዙሪያ በዋናው ግቢ ኦዲቶሪየም አዳራሽ ውይይት አደረጉ፡፡

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንግዶች ወደ ውቧ ባህር ዳር እና ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንኳን በደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያለባቸውን ታላቅ የሀገር ኃላፊነት ከተቀበሉ በአጭር ጊዜ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ለመጉብኘት በመምጣታቸው አመስግነው ዩኒቨርሲቲው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ያከናወናቸውን እና እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት በአጭሩ ገልፀዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ካላቸው የተጣበበ ጊዜ የሴት ተማሪዎችንና መምህራንና ሰራተኞች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለመካፈል እና ያላቸውውን የዳበረ የስራና የህይወት ተሞክሮ ደግሞ ለማካፈል በዩኒቨርሲቲው በመገኘታቸው በራሳቸው እና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስም ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ስርዓተ-ፆታ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሚል ርዕስ አጠር ያለ ንግግር አቅርበዋል፡፡ በንግግራቸውም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የዳሰሱ ሲሆን ተጨማሪ ስራም እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በንግግራቸው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተለያዩ የጥናት ምስኮች ላይ ያተኮሩ ተቋማት ግቢዎች  እንዳሉት አውስተው ከተማዋን የዩኒቨርሲቲ ከተማ እንዳደረጋትና በዚህም ምክንያት UNESCO የትምህርት ከተማ ብሎ እንደሰየማት አስታውሰዋል፡፡ በተያያዘም የዩኒቨርሲቲውን የወደፊት አደረጃጀት የሚያሳይ የፖሊ-ፔዳ ማስተር ፕላን አሳይተዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በመቀጠል የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ በቁጥር እና በመቶኛ አመልክተው ከርቀት ትምህርት ውጭ ተሳትፏቸው አናሳ መሆኑን ጠቁመው የፕሬዚደንቷ እገዛ ከታከለበት በዚህ ዙሪያ የተሸለ ስራ መስራት እንደሚቻል የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ካሉ ሴት ተኮር ድጋፎች አንፃር የህፃናት ማቆያ የሚጠቀስ ሲሆን በ2012 ዓ.ም. በሁሉም ግቢዎች ተመሳሳይ ማቆያዎች እንዲኖሩ እቅድ እንደተያዘ ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ መርሃ ግብር የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ሚንስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ለፕሬዚደንቷ የተደረገው አቀባበል እና በአዳራሹ የተገኘው ታዳሚ ከዚህ በፊት በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ወቅት እንዳላዩት ተናግረው ፕሬዚደንቷን እንኳን ደህና መጡ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሂሩት አክለውም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰራቸው ስራዎች ከቀረበውም በላይ እንደሆነ አውስተው የሴት መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ማህበር እንዲቋቋም በማድረግ ሴቶች ለመብታቸው እንዲታገሉ ያደረገ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወደ መድረክ በመውጣት ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን በጣና ፎረም ምክንያት እንደሚያውቁት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚደንቷ አክለውም የመጀመሪያ የስራ ህይወታቸው በትምህርት ሚንስትር እንደነበር አስታውሰው ከዚያም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ በሚመስለው የዲፕሎማሲው ዘርፍ አገራቸውን ለረጅም ጊዜ እንዳገለገሉ ገልጸው ጉዟቸው የፆታም ሆነ ሌሎች ተግዳሮቶችን በመፋለም የተሞላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በንግግራቸውም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ከታች ጀምሮ ሊሰራ እንደሚገባ በአፅንኦት አሳስበው የተለያዩ መሰናክሎችን አልፋ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባችውን ሴት ልጅ ዲግሪዋን ይዛ መውጣት እንድትችል ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም  ከተሳታፊ ሴት መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ፕሬዚደንቷ የተነሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ ለሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደሚያሳውቁ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በራሱ ሊፈቱ የሚችሉትን ችግሮች እንደሚቀርፍ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት አካታችና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆናቸው መሰረታዊ መሆኑን ገልፀው በሴቶች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች የዜሮ ቶለራንስ ፖሊሲ መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የሴቶች ጉዳይም የሁሉም ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ኃላፊነቱን በመውሰድ ተጨበጭ ለውጥ እንዲመጣ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁም ከወሬ ያለፈ ሃሳብ በማፍለቅ የሴቶችን ጉዳይ ወደ ማሃል በማምጣት ችግሮችን ለመቅረፍ መሰራት እንዳለበት ተናግረው ቀጣይ አቅጣጫዎችንም እንደሚከተለው ጠቁመዋል፡፡

1. የሴቶችን አስተዋፅኦ ብዛትና ጥራት ለማሳደግ ከሌሎች የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጉድኝት መሰራት፤

2. የማማከር ስራ/Mentoring- በስፋት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው ወጣት ሴቶችን ለማበረታታት እና በራስ መተማመናቸውን ለማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

3. በዩኒቨርሲቲው ለሴቶች የሚሰጠው የአጋዥ ስልጠና/ Tutorial/ አገልግሎት በውጤት ያልተደገፈ በመሆኑ ሂደቱን በመፈተሸ እና በማሻሻል ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

4. ሴቶች የነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ስራዎች እንደሚሰሩና ጅምሮችም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ለአካዳሚክ አመራሩ በትምህርት ጥራት ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ የጥራት አስተዳደር ከከፍተኛ ትምሀርት ጥራት አግባብነት አጀንሲ (HERQA) ጋር በመተባበር ለአካዳሚክ አመራር አካላት ለአራት ቀናት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የስልጠናው ዋና አዘጋጅ የአጠቃላይ ጥራት አስተዳደር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ እጅጉ መምህራን ጥራቱን የጠበቀ የመማር ማስተማር ስራ እንዲሰሩ ለማገዝ ይህ ስልጠና መዘጋጀቱን ገልፀው በስልጠና መክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት ዘመናዊ ትምህርትን ከምዕራባውያን እንደመቀበላችን ምንም እንኳን ከፍተኛ ትምህርት ከዓለም አንፃር እድሜው አነስተኛ ቢሆንም በሃገራችን ለትምህርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት ከምዕራባውያኑ አንፃር የዘገየ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ አክለውም ስልጠናው  ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበው እንደዋና ዓላማ በአመራር ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲው አከላት የሚያነሱትን የአመራር አቅም ግንባታ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ታልሞ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልፀው መሰል ጥያቄዎች ከዚህ በኋላ  እንደማይኖሩ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሌላው የስልጠናው ዋና አላማ  ደግሞ  ተማሪዎችን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪነት ያላቸው እንዲሆኑ፣ ብሎም ችግር ለመፍታት የሚያስችል በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ሆነው እንዲመረቁ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ስራ አመራሩ የመሪነት ድርሻውን በአግባቡ እንዲወጣ ይችል ዘንድ ስንቅ ለመስጠት  እንደሆነ ዶ/ር ፍሬው መቁመዋል፡፡

ስልጠናው ከመጋቢት 19 እስከ 22 2011 ዓ.ም. ድረስ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

የትያትር ሰልጣኞች ተመረቁ

በትዕግስት ዳዊት

ሰላሣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል አባል ተማሪዎች  በመሉዓለም የባህል ማዕከል የትያትር አዘጋጅ በሆኑት አቶ ደሳለኝ ድረስ የሰማኒያ ሰዓት የትያትር ስልጠና ወስደው ተመረቁ፡፡

ሰልጣኞች ከትያትር ትወና በተጨማሪ የ(ሜክ አፕ) ስልጠና መውሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ  ያሉ ሆነው የትያትር ፍቅር እና የትወና ፍላጎት ያላቸው ብቻ ተመርጠው በስልጠናው እንደተሳተፉ ተነግሯል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የሙሉዓለም የባህል ማዕከል የትያትር አዘጋጅ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ድረስ የተለያዩ ድርሰቶችን በግል እና በጋራ የደረሱ ሲሆን  በተጨማሪም የቲያትር አዘጋጅ በመሆንም ስፊ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ሰልጣኞችም በሙያው እውቀትና ልምድ ባላቸው ባለሙያ በመሰልጠናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ጭውውቶች፣ትያትሮች፣የስነ ግጥም ስራዎች እና ማይም ( ድምጽ አልባ ተውኔት ) በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል ተዋንያን ለታዳሚወች ቀርቧል፡፡

ተቋርጦ የነበረው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል በየሁለት ሳምንቱ ይካሄድ የነበረው የስነ-ጽሁፍ ምሽት ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ እንደ በፊቱ እንደሚካሄድ ተገልፆ ማነኛውም ፍላጎቱ ያለው ሁሉ በፕሮግራሙ መታደም እንደሚችል ጥሪ ቀርቧል፡፡  

School of Law, Bahir Dar University, in collaboration with international arbitrators, Mr. Alexander Monro and Ms. Stephanie Mobnu from the international law firm of Fresh fields Bruckhaus Deringer, has organized short training for the staffs on the area of international commercial arbitration and alsoa workshop from 18-22 February, 2019 forthe postgraduate students who will participate on behalf of BDU at the 26th Willem C. Vis International Commercial Arbitration Moot Court in German and Austria that attracts 378 universities from all over the globe.

 

የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡

በትዕግስት ዳዊት

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኘው የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለሶስተኛ ጊዜ አስመረቀ፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መሬት አስተዳደር ዳይሬክተር ዶ/ር በላቸው ይርሳው ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን የቀለም እና የተግባር ትምህርት ወደ ተግባር የሚተረጉሙበት እና ከራሳችው አልፎ ህብረተሰባቸውን የሚያገለግሉበት ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የኪነ ህንጻ ትምህርት ትዕግስት እና ፈጠራ የሚጠይቅ በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያሳደጉትን የፈጠራ ክህሎት የበለጠ አጎልብተው እራሳቸውን ጠቅመው ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉበት አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር በላቸው አክለውም የኪነ ህንጻን ሙያ የሚጠይቅ ስራ የሚሰሩ የፌዴራል፣የክልል የግልም ሆነ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሃብት እና እውቀት ፈሶባቸው የሰለጠኑ ተመራቂዎችን በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ እንደተናገሩት የሚገነቡት ከተሞች ብሎም ሀገራት የሚመስሉት የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎችን በመሆኑ ለከተሞች ውበት፣የኑሮ ምቹነት ፣ቀጣይነት፣ወጭ ቆጣቢነት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ቀጥለውም አሁን ትልቅ የኪነ-ህንፃ ጥበብ የሚታይባቸው የሃገራችን ቅርሶች የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባቸው ጊዜ ሲሆን መታደግ የሚቻለውም በእውቀት እና በጥበብ በመሆኑ ተመራቂዎች ያላቸውን እውቀት እና ጥበብ በተቋርቋሪነት መንፈስ በመጠቀም ከመፍረስ እንዲታደጓቸው አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች የኢትዪጵያን ቅርሶች፣መልክምድሮች፣እንስሳት፣እጽዋት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ሌሎች የሌሏቸው መለዮወቻችንን የንድፋቸው ማስጌጫ መጠበቢያ ቅመም በማድረግ እንዲጠቀሙባቸው አሳስበው አለም ከደረሰበት እድገት አንጸርም ዘመኑን የዋጀ ንድፍ መስራት እንደሚገባቸው ተናግረው ከሁሉም በፊት ግን ህሊናቸውን እና ፈጣሪያቸውን ዳኛ አድርገው የሙያ ስነምግባር በተላበሰ መልኩ እንዲሰሩ በአጽንኦት መክረዋል፡፡ በመጨረሻም ተመራቂዎች በሙያቸው ስኬታማ በመሆን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ብሎም የውድ ሃገራቸውን ስም የበለጠ በበጎ  እንዲታወቁ የበኪላቸውን ያደርጉ ዘንድ አደራ ብለዋል ፡፡

 

በምረቃ በርሃግብሩ የተገኙት አርክቴክት አበበ ይመኑ የረጂም ጊዜ የህይወት ተሞክሯቸውን እና የስራ ልምዳቸውን ለተመራቂዎች ያቀረቡ ሲሆን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትምህርት ክፍል ደረጃ የሚሰሩት የተማሪዎች ፕሮጀክቶች ደረጃቸው ከፍ እንዲል መሰራት እንዳለበት ጠቁመው በተጨማሪም በሙያው ትልቅ ስም ያላቸው አርክቴክቶች ያላቸውን የስራ ልምድ፣ የፈጠራ ችሎታቸውንና ክህሎት ማካፈል የሚችሉበት መርሃግብር ቢዘጋጅ ጥሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ አበበ ይመኑ በመጨረሻም የኪነ ህንጻ ትምህርት በባህሪው የተለየ ክህሎት እና የተለየ ከባቢያዊ ሁኔታ የሚፈልግ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ እና ከ1ኛ-5ኛ ለወጡ ተማሪወች ሽልማት ተስጥቷል፡፡ ከሴቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ቃልኪዳን ጥበቡ እንዲሁ ሽልማት የወሰደች ሲሆን ተማሪ በረከት ምትኩ 3.76 በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የዘንድሮው ምርቃት በትምህርት ክፍሉ ሶስተኛው ሲሆን 22 ወንዶች እና 7 ሴቶች በድምሩ 29 ተማሪወች ለምረቃ በቅተዋል፡፡

በእለቱ በተማሪወቹ የተሰሩ  የኪነ ህንጻ ንድፎች አውደ ርዕይ በመርሃ ግብሩ ለተገኙ ተሳታፊወች እና ተመራቂ ቤተሰቦች ተጎብኝተዋል፡፡

    

 

 

ሰባተኛው የአማርኛ ቋንቋና የባህል ዘርፎች አገር አቀፍ አውደ ጥናት በዩኒቨርሲቲው ተካሄደ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም (አቋማተ) ሰባተኛውን የአማርኛ ቋንቋና የባህል ዘርፎች አገር አቀፍ አውደ ጥናት መጋቢት 6 2011 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ፔዳ ግቢ አካሄደ፡፡ መርሃ-ግብሩ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና ለፕሮግራሙ አዘጋጆች የምስጋና መልዕክታቸውን አስተላልፈው አማርኛ ቋንቋን ከዘመኑ ጋር ለማስኬድና ከአገር አቀፍ ደረጃ በዘለለ መልኩ ለአፍሪካ ህብረት የመግባቢያ ቋንቋ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው ከማዕከሉ ጋር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ አክለውም በአሁኑ ወቅት አማርኛ ቋንቋንና ባህልን ለማበልፀግ የሚያግዝ “ Online Dictionary” እና የመማሪያ “Application” ስለሌለ ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በግንባር ቀደምትነት መስራት እንዳለበት በአንክሮ ተናግረው የአውደ ጥናቱ መካሄድም የተጠቀሱትንና መሰል ክፍተቶች ለመሙላት የማንቂያ ደወል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የዓውደ ጥናቱን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከሰጣቸው ስድስቱ እንቁ ሙህራን አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ “ቋንቋ የሰው ሰውነት ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተነስተው የቋንቋ መስፋፋት ከግለሰብ ጀምሮ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ፣አገር እንደ አገር እንዲያድግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውና የበሰለ ቋንቋ ከሌለ ሀሳብም እንደሚቀጭጭ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በማስከተል የሰው ልጅና የቋንቋ ትስስር ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው በማስረጃ አስደግፈው ሰፊ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ሳይንሳዊ ቋንቋ መጠቀም ደረጃን ከፍ ሲያደርግ የሳሳ ቋንቋና የወረደ ቃላት መጠቀም ደግሞ በአንፃሩ የእውቀትን ዲካ ስለሚለካ የአውደ ጥናቱ ዓላማ የቋንቋን እድገት ለማምጣትና ባህልን ለማስተዋወቅ የሚጠቁሙ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ቋንቋችንና ባህላችን ያሉበትን ሁኔታ አብጠርጥረው በማሳየት አንዱ ከአንዱ የእውቀት ሽግግር የሚያደርግበት መድረክ እንደሚሆን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች በተለያዩ ምሁራን ቀርበው በቀረቡት ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

Pages