ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (International Livestock Research Institute) /ILRI/ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (International Livestock Research Institute) /ILRI/ ጋር አብሮ ለመስራት በፕሬዘዳንት ጽ/ቤት በ19/12/14 ዓ.ም. የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ አሁን እስከ ደረሰበት ደረጃ ያለውን ዋና ዋና ሂደት፣ራዕዩን፣ተልዕኮውን እና በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ ፕሮግራሞች እንዲሁም የሰው ኃይሉን አጠቃላይ እያከናወነ ያላቸውን አኩሪ ተግባራት የሚያሳይ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (International Livestock Research Institute) (ILRI) ዋና ዳይሬክተር Dr. Jimmy Smith ተቋማቸውን የሚያስተዋውቅ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘና የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር Dr. Jimmy Smith ሲሆኑ ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት የመጡት ልዕክና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ቤተ-ሙከራዎችን ጨምሮ ምን እንደሚመስል እንዲሁም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝ ሆስፒታል በስፋት ጎብኝተዋል፡፡
የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር በሆኑት በፕሮፌሰር የሽጌታ ገላው መሪነት ኮሌጁ ሲጎበኝ በቅርቡ ስራ የሚጀምረውና በአገር አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ጣና የምርምርና ዳያግኖስቲክ ማዕከል የተሰኘው በውስጡ 237 ክፍሎችን የያዘ ሲሆን ለወደፊት በርካታ ችግር ፈች የምርምር ዘርፎች የሚከናወኑበት መሆኑን ከጉብኝቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በዚሁ ኮሌጅ በቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ ስም የተሰየመውን ዘመናዊ ቤተ-መፅሓፍት፣ ንፁህ የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ፣ በዚህ ዓመት የሚመረቁት 160 ሐኪሞች የሚኖሩበት ዶርሚተሪ እና የመሳሰሉት ዋና ዋና የስራ ክፍሎች ተጉብኝተዋል፡፡
በሙሉጎጃም አንዱዓለም