በሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ስራዎች ትግበራ ላይ ውይይት ተካሄደ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ስራዎች አተገባበር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት አካሂዷል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ኃይሉ አበበ እንደገለጹት የዛሬው ውይይት ከአንድ አመት በፊት ዩኒቨርሲቲው ከKHUNE ፋውንዴሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ እንደነበር አስታውሰው የሰነዱ ዋና ጭብጥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ላይ በሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ዘርፍ ክፍተት በመኖሩ ጥህን ለመቅረፍ የትምህርት ፕሮግራሞች ሊከፈቱ ይገባል የሚል ነበር፡፡ በስምምነት ሰነዱ በጋራ ለመስራት ከተስማማንባቸው ሰባት ዋና ዋና ዘርፎች ውስጥ ምን ያክሉ ወደ ተግባር ገብተዋል ምን ምን ስራዎችስ በስምምነቱ መሰረት ተከናውነዋል የሚለው ቀርቦ ውይይት የተደረገበት መሆኑን አቶ ኃይሉ አበበ ተናግረዋል፡፡
ባለፍው አመት ግንቦት ወር ላይ KHUNE ፋውንዴሽን ሙሉ ወጭውን ሸፍኖ በተዘጋጀው መድረክ በርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተደርገ ሲሆን መንግስትም የፖሊሲ ሰነድ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበት፤ በሰነዶች ላይ ግብአት የተሰበሰበበትና ምሁራንም አስተያየት የሰጡበት መድረክ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አክለውም በርካታ የምርምር ስራዎችንም በጋራ በመስራት ላይ እንደሚገኙና በማህበረሰብ አገልግሎትም ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ስራ እንደተገባ ገልፀዋል፡፡ KHUNE ፋውንዴሽን አቅም መገንባት አንዱ የውስጥ እቅዱ ስለሆነ የሦስተኛ ዲግሪ በሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ትምህርት በዚህ አመት እንዲጀመር የስርአተ ትምህርት ቀረጻ እና በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ተማሪዎቻችን የስራ ልምምድ በሚወጡበት ጊዜ ሙሉ ትኩረታቸውን ልምምዱ ላይ እንዲያደርጉ ወጫቸውን መሸፈን ላይም ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑና በአፍሪካም እራሴን ግንባር ቀደም አደርጋለሁ ብሎ ባስቀመጠው ራዕይ ልክ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ከውጭ አጋር አካላት ጋር የሚያደርጋቸው የስራ ስምምነቶች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል ምሁሩ ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተምረው የሚወጡ ተማሪዎች አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን እየቀረጸ በማስተማር ላይ መሆኑን ያሳየበት ሲሆን ይህም የከፍተኛ አመራሩን ቁርጠኝነትና ድጋፍ የሚያሳይ ነው ብለዋል አቶ ኃይሉ አበበ፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ባልተቀላጠፈ የሎጀስቲክስ ስርዓት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማረጋገጥ አይቻልም፤ የግብርና ዘርፉ ግብዓቶች፣ የፋብሪካ ማምረቻ ጥሬ እቃዎች እና የጤና ተቋማት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን እና መድሃኒት ማምረትና ማከፋፈል፣ እንዲሁም አጠቃላይ የንግድ ስርዓቱ ያለ ሎጀስቲክስ እንደማይታሰብ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፤ የኤልያስ መልአክ ፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤሊያስ መላክ እና የKHUNE ፋውንዴሽን የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡