የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ሶስተኛውን ሀገራዊ አውደ ጥናት አካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም አይበገሬ ማህበረሰብን መገንባት (Building Disaster Resilient Community) በሚል መሪ ቃለ ሶስተኛውን ሀገራዊ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡አደጋን ለመከላከል መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሁሉም በዘርፉ ያሉ አካላት አይበገሬ ማህበረሰብን ለመፍጠር መንቀሳቀስ እንዳለባቸው እና ሁሉም የዓለም ህዝብ ፊቱን ወደ አደጋ መከላከል ማዞር እንዳለበት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አብርሃም መብራት ተናግረዋል፡፡የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ላይ የሚታዩ የፖሊሲና መሰል ክፍተቶችን በመለየት አቅም የማጐልበት እና የምርምር ሥራዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስወገድ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኢንስቲትዩት በ2005 ዓ.ም በማቋቋም በመማር ማስተማር ሆነ በምርምር ዘርፉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ወቅት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ላይ የልህቀት ማዕከል ለመሆን በመሥራት ላይ እንደሆነ እና ከተለያዩ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ አጋር አካላት ጋር በመማር ማስተማሩ እንዲሁም በምርምር ሥራዎች ላይ አብሮ እየሰራ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ለምሳሌ ያክልም ከUniversity of Arizona (USA)፣ University of Jaume (Spain), Wageningen University (The Nether Lands), University of cape town (SA), UNDP, USAID, DRMFSS, ACCRA, CORDID, OXFAM, REDCROSS እና FEPRA ጋር በጋራ አየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2017 ዓ.ም አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አስር ግንባር ቀደም የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ለመሆን ራዕይ በማስቀመጥ እየሰራ እንደሆነ እና ለስኬቱም የተለያዩ የምርምር ተቋማትን በማቋቋም የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሆነ እና ከምርምር ማዕከላት በተጨማሪ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፍ የምርምር ሥራዎች እየሰራ እንደሆነ የተናገሩት በመርኃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዋሴ አንተነህ ናቸው፡፡ዳይሬክተሩ አክለውም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሉም ኮሌጆች፣ ፋኩልቲዎች፣ ኢንስቲትዩቶች ዓመታዊ አውደ ጥናት እያካሄዱ እንደሆነ እና እንደዚህ ያሉ መርኃ ግብሮች ልምድ የሚገኝባቸውና የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ ወደ ግብ እንዲያመራ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻም የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ተቋም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በምግብ ዋስትና፣ አደጋን ከመቀነስ አኳያ እና የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ምርምሮችን በማከናወን ላየ እንደሆነ እና የሚሰሩት የምርምር ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ በመሆናቸው ኢንስቲትዩቱ የበለጠ መስራት እንዳለበት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መመስረት እንደሚገባና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የአደጋ ስጋትን መቀነስ ላይ ሁሉም አካል በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅና ለሀገራችንም ትልቁ ስጋት የአየር ንብረት ለውጥ እንደሆነ ለዚህም ማሳያ በሀገራችን ለተከታታይ ሁለት ዓመት የዘለቀው የድርቅ አደጋ በአየር ንብረት ለውጥ የመጣ እንደሆነ የገለፁት በመርኃ ግብሩ ላይ ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ፣ ደንና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር በላይነህ አየለ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙቀት አማቂ ጋዞች ልዕቀት መጨመር፣ የባሕር ጠለል ከፍታ መጨመር፣ የሙቀት መጨመር፣ የጐርፍ አደጋ፣ የድርቅና የሰደድ እሳት አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነ ጠቁመው ይህን የዓለም ስጋት የሆነን የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ሕዝብ በጋራ በመሆን መከላከል እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

Share