የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ህብረት ተቋቋመ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ተማሪዎች ህብረት ተቋቋመ፡፡

 

ህብረቱ በትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች ተዘጋጅቶ በነበረው የአዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ዝግጅት ላይ ተመስርቷል፡፡

 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ትምህርት መምህር አቶ ሰሎሞን ሙሉ በምስረታው ላይ እንደተናገሩት የክለቡ አላማ ተማሪዎች በጋራ የመስራት ልምድ እንዲያዳብሩና በፋኩልው ስር ከዚህ ቀደም የነበረውን የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ተማሪዎች ማህበር ከመጥፋት ለመታደግና የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች ክህሎታቸውን የሚለዋወጡበት፣ ችግራቸውን በራሳቸው የሚፈቱበት፣ ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበትና የጋዜጠኝነትን ስራ ቀድመው የሚለማመዱበት መድረክ ለመፍጠር እንደሆነ ገልፆአል፡፡

 

በተጨማሪም ህብረቱ “ራስን ፍለጋ” በሚል ርዕስ ዘወትር ሀሙስ ምሽት በጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ተማሪዎች ህብረት የሚከናወነውን መርሃግብር አጠናክሮ ለመቀጠልና ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው አሻራቸውን አሳርፈው ለቀጣይ  ተማሪዎች የሚያስተላልፉት መድረክ እንደሚሆን አቶ ሰሎሞን አስገንዝበዋል፡፡

 

በምስረታው ላይ የህብረቱን ስራ ለማስጀመር 10 አባላት ያሉት ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ፍትሃዊ የሆነ አሰራር እንዲኖርም ከአዲስ ገቢ ተማሪዎች፣ ከ2ኛ አመት እንዲሁም ከተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ ምርጫ ተደርጓል፡፡

 

በመጨረሻም በቀጣይ ህብረቱን ህጋዊ ለማድረግና ስለወደፊት የአሰራር ሁኔታዎች ለመምከር ተከታታይ ውይይቶች ይደረጋሉ ተብሏል፡፡ ለህብረቱ በሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ትምህርት ክፍሉም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንደሚያደርጉና በግልም የድጋፍና የማስተባበር ስራ እንደሚሰሩ መ/ር ሰሎሞን ቃል ገብተዋል፡፡

 

 

 

 

 

Share