የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ መምህራንና ተማሪዎች ህብረት ተመሰረተ

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ መምህራንና ተማሪዎች ህብረት መጋቢት 12, 2ዐዐ6 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ የህብረቱ መመስረት ዋናው አላማው በፋኩልቲው በሚገኙት አራቱም የትምህርት ክፍሎች በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ፅሁፍ አማርኛ ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ ፅሁፍ፣ በባህልና ጥናትና ጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍሎች መምህራንና ተማሪዎች መልካም ግንኙነት መፍጠር ነው፡፡

የፋኩልቲው ዲንና የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ ዶ/ር ስዩም ተሾመ እንደተናገሩት ህብረቱ በተማሪዎችና በመምህራን መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ከማስቻሉም በላይ በመደጋገፍ የተጠናከረ ስራ እንድንሰራ ያስችለናል ብለዋል፡፡ በህብረቱ መመስረት የተሰማቸውን ደስታ በመክፈቻ ንግግራቸው የገለፁት ዶ/ር ስዩም አክለው እንዳሉት የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ የንባብ ባህልን ማዳበር፣ ማስታወቂያና ዜናዎችን መስራት፣ የባህል ጥናት ማድረግ፣ ስነፅሁፎችን ማዘጋጀትና የመሳሰሉትን ህብረቱ ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው ተግባራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ፋኩልቲው ባደረገው የህብረት ምስረታ መርኃ ግብር ላይ መነባንብ፣ አጫጭር ግጥሞች፣ ቀረርቶ፣ ዜናና የመሳሰሉት አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶች በተማሪዎች ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም ውይይት ተደርጐ መርኃ ግብሩ የተጠናቀቀ ሲሆን ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰንዝረው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዝግጅቱ የተገኙት ዶ/ር ዓቢይ ይግዛው የ3ዐ ዓመት የስራና የህይወት ልምዳቸውን ለተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡ ለረጅም አመታት በመምህርነት ሙያ በማገልገል ላይ ያሉት ዶ/ሩ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ጀምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ፣ አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ትውልድን በእውቀት ገንብተዋል እየገነቡም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በፋኩልቲው የመጀመሪያ በዩኒቨርሲቲው ደግሞ ሁለተኛው ፕሮፌሰር ለመሆን የመጨረሻ ምእራፍ ላይ የሚገኙት ዶ/ር ዓቢይ ልምዳቸውን ሲያካፍሉ እውቀት ብዙ ጥረት ስለሚያስፈልገው ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ለለውጥ መነሳት እንዳለባቸው ጠቁመው ከመፎካከር ይልቅ መተባበር የተሻለ መሆኑን ተናግረውል፡፡ ዶሩ ምን ያስደስተዎታል ተብለው ሲጠየቁ ማንበብ፣ ለትውልድ የሚተርፍ ስራ መስራትና መምህር እንደሆንኩ ብሞት ያስደስተኛል ብለዋል፡፡

Date: 
Tue, 07/15/2014
Image: 
Place: 
Bahir Dar University
Share