STEM Center አስመረቀ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል / STEM Center / ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን አስመረቀ
===================================================================
በሙሉጌታ ዘለቀ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል / STEM Incubation Center/ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተወጣጥተው በበጋ ወራት ሲሰለጥኑ የነበሩ ሴት 24 ወንድ 34 በአጠቃላይ 58 የ12ኛ ክፍል ሰልጣኝ ተማሪዎችን ሐምሌ 14/2011 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ በማዕከሉ ግቢ አስመርቋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች በአራት አመት ቆይታ የሰሯቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንግዶች ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱም በተማሪዎች የተሰሩ ተንቀሳቃሽ ሮቦቶች እና ለህፃናት መማሪያ የሚሆኑ የሞባይል ሶፍትዌሮች እንዲሁም ሌሎችም የፈጠራ ስራዎች በምረቃው ላይ ለተገኙ የመንግስት መስሪያቤት ሀላፊዎች እና ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ለተማሪ ወላጆች በተግባር አሳይተዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ሲስተር ኤደን አምሳሉ የምረቃ ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱ ሲሆን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባህር ዳር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከልን ለማቋቋም ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ በ2004 ዓ.ም ይህን ማዕከል እውን እንዲሆን አድርጓል ብለዋል፡፡ በዚህ ማዕከል የሚሰለጥኑ ተማሪዎች በከተማችን ካሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሳይንስ ትምህርት ዝንባሌ ያለቸውና በውጤታቸውም የተሸሉ ተማሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡ ሲስተር ኤደን አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሚሰራቸው የማህበረሰብ አገልግሎት ውስጥ ይህ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል / STEM Center / አንዱ መሆኑንና ሀገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ፈጣን ሽግግር ማዕከሉ በቴክኖሎጂ ፈጠራ በሳል የሆነ የሰው ሀይል በማቅረብ በኩል አስተዋፃ ያበረክታል ብለዋል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዶ/ር ሰብስበው አጥቃው እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም አቤ እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር እሰይ ከበደ እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ርዕሳ መምህራን ለማዕከሉ አጋር አካላት፣የፈጠራ ስራ በመስራት ለተወዳደሩ ተማሪዎች ፣ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ለበጎ ፈቃድ ተሳታፊ ተማሪዎች እንዲሁም ለማዕከሉ ጠንካራ ሰራተኞች የማበረታቻ ሽልማትና ሰርተትኬት ሰጥተዋል፡፡
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙሉዓለም አቤ የ12ኛ ክፍል ሰልጣኝ ተማሪዎችን መርቀው ለተመራቂ ተማሪዎችም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተማሪ ወላጆች ካሁን በፊት የነበሩና በቀጣይም በማዕከሉ ተማሪዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን የጠየቁ ሲሆን ለጥያቄዎችም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር እሰይ ከበደ ማብራሪ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የቀድሞው የማዕከሉ ዳይሬክተር የነበሩት አሁን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው በተማሪ ወላጆች ለቀረቡ ስጋቶች ናቸው ያሏቸውን ጥያቄዎች አብራርተው ወላጆች የልጆቻቸውን ስብዕና መከታተል እንዳለባቸው እና የተበላሸ ስብዕና ያላቸውን ተማሪዎች ይህ ማዕከል እንደማያስተናግድ በአፅዕኖት ተናግረዋል፡፡ተመራቂ ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲ በሚገቡበት ወቅት የመጀመሪያ ምርጫቸው እንደሚጠበቅላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምምነት ላይ መደረሱን ለተመራቂዎች አብስረዋል ፡፡

በእለቱ በግቢው ውስጥ የሚገኙና ህብረተሰቡ ለመዳኒትነት የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ እፅዋቶችን ጉብኝት የተሄደ ሲሆን ስለተቋሙ አጠቃላይ ገለፃ በተማሪዎችና በማዕከሉ ዳይሬክተር ተሰጥቷል፡፡