OXFAM-GB የምክክር መድረክ

OXFAM-GB የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት የስራ ጊዜውን በማጠናቀቁ በአማራ ክልል የነበረውን ቆይታ በማስመልከት የምክክር መድረክ በባህር ዳር አካሄደ፡፡
-----------------------------------------------------------------------------------
በሙሉጌታ ዘለቀ
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ OXFAM-GB ተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ አዊ ብሄረሰብ ዞን፣ ዳንግላና ጓንጓ ወረዳዎች ውስጥ ̋Empowering women and improving livelihood through honey value chain ̋ በሚል ርዕስ በማር እሴት ሰንሰለት ዙሪያ ጥናቶችን አስጠንቶ ሴት አርሷደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እና የመንግስት አካላት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ ምክክር አደረገ፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በአማራ ክልል የOXFAM-GB ፕሮጅክት ሀላፊ የሆኑት አቶ አለሙ አድማሴ ስለ ፕሮጅክቱ አላማ ከምን እንደተነሳና ምን ለማድረግ እንደታሰበ ለታዳሚው በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል፡፡
 
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዩ ሽፈራው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከውጭ ወደ ሀገራችን የሚገቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በቀላሉ በሀገራችን እንዲመረቱ በማድረግ ሂደት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው በማር ምርት ሰንሰለት ለሚሰሩ ተቋማት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በሰልጣኞች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስልጠና እና የአቅም ግንባታ ላይ ዩኒቨርሲቲው እንደሚሳተፍ ተናግረው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡
 
OXFAM-GB የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በዋናነት ሴት አርሷደሮች በማር ምርት ሰንሰለት ላይ ያላቸውን እምቅ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙበት ከማድረግም በላይ በማር ምርት ሰንሰለቱ እንዲሳተፋ በማድረግ፣ የንብ ማነብ ሂደት ምን እንደሚመስል ስልጠና በመስጠት፣ የማር ማጣራት ሂደትን በማሳየት፣ ሰምን በማጣራትና ወደ ገበያ በመቅረብ ላይ ሲሰራ መቆየቱ በመድረኩ ላይ የተነገረ ሲሆን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን የንብ ማነብ ክህሎትን በማሳደግና የተለያዩ የስልጠና ሞጅሎችን በማዘጋጀት ለሙያው ከፍተኛ አስተዋፆ እንደነበራቸው ተግልጿል፡፡
 
በአሁኑ ሰዓት OXFAM-GB የተሰኘው ተቋም በአማራ ክልል ላይ የነበረውን ቆይታ በማጠናቀቁ ምክንያት እስካሁን የተጓዘባቸውን የስራ ጊዜያት ተከትሎ ጥናቶችን አስጠንቶ በእለቱ ለውይይት ቀርቧል፡፡ ጥናቶቹም ከፕሮጀክቱ ትግበራ በኋላ በንብ ማነብ ሰንሰለቱ ላይ የመጣውን ውጤት ፣ የንብ ማነብ ግብዓቶችን ለማቅረብ የነበሩ መልካም አጋጣሚዎች እና ተግዳሮቶች በሚሉና በንብ ማነብ ዙሪያ የተለያዩ ሴት አርሷደሮች ባጋጠሟቸው ችግሮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ነበሩ፡፡
 
በውይይቱ ላይ እንደዋና የውይይት ሀሳብ ሆኖ በተወያዮች የቀረበው የንብ ማነቢያ ቦታ ነው፡፡ ማነቢያ ቦታዎች የሰብል እርሻ አቅራቢያ በመሆናቸው በሰብሎች ላይ በሚረጭ ኬሚካል ምክንያትና በሌሎች ውስጣዊ እና ውጫዊ በሆኑ በርካታ ምክኒያቶች የማር ምርት የተፈለገውን ምርት ማግኘት እንዳልተቻለ ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ የሴት አርሷደሮች ቁጥር እስከ ሦስት ሽህ እንደሚደርስ በውይይቱ ላይ ጥናት አቅራቢና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብይ መንክር ተናግረዋል፡፡
 
በመጨረሻም ተወያዮች የመጡበትን ወረዳ በሚመለከት በቀረቡ ጥናቶች ላይ ትክክል የሆነውንና ይቀራል ያሉትን ሀሳብ በቡድን በመሆን ገምግመዋል፡፡