Appointment

ዶ/ር ተስፋየ ሽፈራው ቦጋለ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ዛሬ የካቲት 19/2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በቅርቡ ሲካሄድ በቆየው የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ተወዳዳሪ ከነበሩት መካከል የላቀ ውጤት ያስመዘገቡትን ዶ/ር ተስፋየ ሽፈራው ቦጋለን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾመ፡፡

 

ዶ/ር ተስፋየ ከሌሎች አራት ዕጩዎች ጋር በተለያዩ መመዘኛዎች ተወዳድረው በአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ በመሆናቸው ቦርዱ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የወሰነ ሲሆን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ነገ የካቲት 20/ 2011 ዓ.ም በይፋ ስራ ይጀምራሉ፡፡

 

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የአመራር ቦታዎችን በውድድር በተመረጡ ኃላፊዎች እንዲያዙ ለማድረግ በጀመረው እንቅስቃሴ በቦርድ በተሰየመ መልማይ ኮሚቴ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ግልጽ በሆነና የተቋሙን ማህበረሰብ ባሳተፈ የምርጫ ሂደት የመረጠ ሲሆን ኮሚቴው የተለያዩ የም/ፕሬዚዳንት ቦታዎችንም በተመሳሳይ መንገድ በተለያዩ መመዘኛዎች እያወዳደረ ሲመድብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በዩኒቨርሲቲው የተሰየመ ሌላ መልማይ ኮሚቴ ሌሎች የአካዳሚክ ክፍሎች ኃላፊዎችን (ዲኖችና ዳይሬክተሮች) ሙሉ በሙሉ ግልጽ በሆነ ውድድር እየመደበ ይገኛል፡፡