78ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል

78ኛው  የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ተከበረ

==============================================

78ኛው  የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል  በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መሰብሰበያ አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ በመክፈቻ ንግግራቸው የድል በዓሉ የወራሪውን ጦር የበቀል ጥም ያከሸፈና የኢትዮጵያዊያንን አይበገሬነት ያሳየ መሆኑን አውስተው ፤ ሚያዝያ 27 ቀን ሁለት ታሪካዊ ድርጊቶች የሚታወሱበት ነው ብለዋል። የመጀመሪያው  ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ለሀገራችን ቀኑ የጨለመበት እና ወረራ የተፈፀመበት ቀን ሲሆን ሌላው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት የአርበኞች ተጋድሎ በኋላ ከማይጨው ሽንፈት አንሰራርታ ከወደቀችበት  በመነሳት የማሸነፍ የሀይል ሚዛኑ ወደ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች የመጣበት ቀን ሆኖ ታሪክ እንደሚያስታውሰው ተናግረዋል፡፡

 

ፕሮፌሰሩ አክለውም ለ78ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የድል በዓል ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን በጥረቶቻቸው ብዙ ፈተናዎች በማለፍ  በነፃነታቸው እና ልዑላዊነታቸው ላይ ምንም ድርድር እንደማያውቁ ያሳዩበት ታላቅ ድል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ያም ሆኖ በወረራው ወቅት ለሀገራቸው  ህይወታቸውን የሰጡ የመኖራቸውን ያህል ጥቂት ባንዳወች እንደነበሩ ታሪክ እንደሚያወሳ ፕሮፌሰሩ ገልፀው በጊዜው የነበሩትን የሀሳብ ልዩነቶች ወደጎን ትተው ኢትዮጵያዊያን እናትና አባት አርበኞች በሀገራቸው ላይ ልዩነት እንደሌላቸው በግልፅ ለዓለም ያሳዩበት ክስተት ነው እንደነበረም ጠቁመዋል ፡፡

 

በትምህርትና ስነ ባህሪ ኮሌጅ የሳይኮሎጂ መምህር የሆኑት አቶ ታምራት ደለለኝ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የትግል አሰላለፍ እና የስነ ልቦና ጥንካሬ፣ ለሀገራቸው ነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያስገኙትን ድል የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በፅሁፋቸውም ጣልያን በወረራው ወቅት ጊዜዊ ድል ያደረጉበትን ቦታ ሳይቀር ለመንገድ እና ለሆቴል ስያሜ እየሰጠ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያዊያን ለተከፈለው መስዋትነት እና ለተገኘው አኩሪ ድል  የሰጡት ትኩረት አናሳ ነው ብለዋል፡፡ የአርበኞች ታላቅ ገድል ዘላለማዊ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ እና አርበኞችና ተጋድሏቸው የበለጠ መጠናትና  መታወስ እንደሚገባ  በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

 

የዚህ ዓመቱ የድል በዓል ሲከበር የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳኝነት አያሌው ፣ አባትና እናት አርበኞች መምህራን፣ ተማሪዎች እና የባህር ዳር ከተማ ወጣት ማህበር አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመውበታል፡፡

 

በዝግጅቱም ታሪኩን የሚዘክሩና የሚያወድሱ የጎዳና ላይ ትርዒቶች ቀርቧል፡፡