ፕሬዚደንቷ ዩኒቨርሲቲውን ጎበኙ

ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የዩኒቨርሲቲው መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ ሴት መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች በተገኙበት መድረክ  በሴቶች በተለይም በዩኒቨርሲቲው ሴት  ተማሪዎች ተግዳሮቶች ዙሪያ በዋናው ግቢ ኦዲቶሪየም አዳራሽ ውይይት አደረጉ፡፡

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንግዶች ወደ ውቧ ባህር ዳር እና ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንኳን በደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያለባቸውን ታላቅ የሀገር ኃላፊነት ከተቀበሉ በአጭር ጊዜ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ለመጉብኘት በመምጣታቸው አመስግነው ዩኒቨርሲቲው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ያከናወናቸውን እና እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት በአጭሩ ገልፀዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ካላቸው የተጣበበ ጊዜ የሴት ተማሪዎችንና መምህራንና ሰራተኞች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለመካፈል እና ያላቸውውን የዳበረ የስራና የህይወት ተሞክሮ ደግሞ ለማካፈል በዩኒቨርሲቲው በመገኘታቸው በራሳቸው እና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስም ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ስርዓተ-ፆታ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሚል ርዕስ አጠር ያለ ንግግር አቅርበዋል፡፡ በንግግራቸውም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የዳሰሱ ሲሆን ተጨማሪ ስራም እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በንግግራቸው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተለያዩ የጥናት ምስኮች ላይ ያተኮሩ ተቋማት ግቢዎች  እንዳሉት አውስተው ከተማዋን የዩኒቨርሲቲ ከተማ እንዳደረጋትና በዚህም ምክንያት UNESCO የትምህርት ከተማ ብሎ እንደሰየማት አስታውሰዋል፡፡ በተያያዘም የዩኒቨርሲቲውን የወደፊት አደረጃጀት የሚያሳይ የፖሊ-ፔዳ ማስተር ፕላን አሳይተዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በመቀጠል የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ በቁጥር እና በመቶኛ አመልክተው ከርቀት ትምህርት ውጭ ተሳትፏቸው አናሳ መሆኑን ጠቁመው የፕሬዚደንቷ እገዛ ከታከለበት በዚህ ዙሪያ የተሸለ ስራ መስራት እንደሚቻል የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ካሉ ሴት ተኮር ድጋፎች አንፃር የህፃናት ማቆያ የሚጠቀስ ሲሆን በ2012 ዓ.ም. በሁሉም ግቢዎች ተመሳሳይ ማቆያዎች እንዲኖሩ እቅድ እንደተያዘ ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ መርሃ ግብር የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ሚንስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ለፕሬዚደንቷ የተደረገው አቀባበል እና በአዳራሹ የተገኘው ታዳሚ ከዚህ በፊት በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ወቅት እንዳላዩት ተናግረው ፕሬዚደንቷን እንኳን ደህና መጡ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሂሩት አክለውም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰራቸው ስራዎች ከቀረበውም በላይ እንደሆነ አውስተው የሴት መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ማህበር እንዲቋቋም በማድረግ ሴቶች ለመብታቸው እንዲታገሉ ያደረገ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወደ መድረክ በመውጣት ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን በጣና ፎረም ምክንያት እንደሚያውቁት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚደንቷ አክለውም የመጀመሪያ የስራ ህይወታቸው በትምህርት ሚንስትር እንደነበር አስታውሰው ከዚያም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ በሚመስለው የዲፕሎማሲው ዘርፍ አገራቸውን ለረጅም ጊዜ እንዳገለገሉ ገልጸው ጉዟቸው የፆታም ሆነ ሌሎች ተግዳሮቶችን በመፋለም የተሞላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በንግግራቸውም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ከታች ጀምሮ ሊሰራ እንደሚገባ በአፅንኦት አሳስበው የተለያዩ መሰናክሎችን አልፋ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባችውን ሴት ልጅ ዲግሪዋን ይዛ መውጣት እንድትችል ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም  ከተሳታፊ ሴት መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ፕሬዚደንቷ የተነሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ ለሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደሚያሳውቁ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በራሱ ሊፈቱ የሚችሉትን ችግሮች እንደሚቀርፍ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት አካታችና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆናቸው መሰረታዊ መሆኑን ገልፀው በሴቶች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች የዜሮ ቶለራንስ ፖሊሲ መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የሴቶች ጉዳይም የሁሉም ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ኃላፊነቱን በመውሰድ ተጨበጭ ለውጥ እንዲመጣ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁም ከወሬ ያለፈ ሃሳብ በማፍለቅ የሴቶችን ጉዳይ ወደ ማሃል በማምጣት ችግሮችን ለመቅረፍ መሰራት እንዳለበት ተናግረው ቀጣይ አቅጣጫዎችንም እንደሚከተለው ጠቁመዋል፡፡

1. የሴቶችን አስተዋፅኦ ብዛትና ጥራት ለማሳደግ ከሌሎች የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጉድኝት መሰራት፤

2. የማማከር ስራ/Mentoring- በስፋት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው ወጣት ሴቶችን ለማበረታታት እና በራስ መተማመናቸውን ለማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

3. በዩኒቨርሲቲው ለሴቶች የሚሰጠው የአጋዥ ስልጠና/ Tutorial/ አገልግሎት በውጤት ያልተደገፈ በመሆኑ ሂደቱን በመፈተሸ እና በማሻሻል ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

4. ሴቶች የነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ስራዎች እንደሚሰሩና ጅምሮችም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡