ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ

ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ እውነታውና አቅጣጫው

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋክልቲ አዘጋጅነት ‹‹ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ እውነታውና አቅጣጫው››  በሚል ርዕስ ተጋባዥ ምሁራን በተገኙበት በዩንቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት ተካሄደ ፡፡

የመወያያ ፅሁፉ በታዋቂው ምሁር ዶ/ር ታየ ብርሃኑ የቀረበ ሲሆን በዋነኛነትም አቅራቢው በኢትዮጵያ የፌደራልዝም አመሰራረትና አተገባበር፣ የፌደራሊዝም ምስረታ መነሻ ሀሳብ ምንነትና አደረጃጀት የሚሉ ሀሳቦች ላይ ተኩረት ያደረገ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ታየ በፅሁፋቸውም ስለ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሲናገሩ በጎሳ ላይ መሰራት ያደረገ መሆኑ በአለማችን ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቷን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ ስለመሆኑ ጥየቄን እንደሚያጭር ገልፀዋል፡፡

ፅሁፍ አቅራቢው አክለውም ሶስቱን የመንግስት ቅርሶች አሃዳዊ፣ ፌደራላዊና ኮንፌዴሪሽን የሚሉትን በመተንተን በኢትዮጵያ እና በሌሎች አገሮች የፌደራሊዝም ባህሪያትና ገፅታ በንፅፅር አቅርበዋል፡፡ በዚህም ከታዳሚው የግልፅነት ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል፡፡