የ2011 ዓ.ም. የተማሪዎች የምረቃ በዓል

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ2011 ዓ.ም. የተማሪዎች የምረቃ በዓልን በድምቀት አከበረ
***************************************************
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ፕሮግራም ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 9750 የሚሆኑ ተማሪዎችን ዛሬ ሀምሌ 13/2011 ዓ.ም. በድምቀት አስመረቀ፡፡
 
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጅክ ኮሚኒኬሽን ም/ ፕሬዚደንት የሆኑት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ በቅርቡ በአሳዛኝ ሁኔታ ላጣናቸው አመራሮች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት አንዲደረግ በማድረግ ፕሮግራሙን ጀምረዋል፡፡ከዚያም ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክ ካስተላለፉ በኋላ በዚህ የምረቃ ዓመት ዩኒቨርሲቲው ለሶስት ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጠ መሆኑን ተናግረው እነዚህ ምሁራን በሃገርና ከሃገር ውጭም በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ከፍተኛ አበርክቶት የሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡ በዕለቱ በተለያየ ምክንያት በአወዱ ባይገኙም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፡ 1. ለዶ/ር ሰገነት ቀለሙ 2. ለማርክ ጌልዶፍ 3. ለፐሮፌሰር ሃንስ ማትሰን እንኳን ደስ አላችሁ ይላል ብለዋል፡፡

 

 

ዩኒቨርሲቲው ከሶስቱ ምሁራን ባሻገር ለሀገር አንድነትና ለሰላም እንዲሁም በሃገራችን ያለውን ለውጥ በማስቀጠል ረገድ ላበረከቱት ልዩ አስተዋፅኦ ለሱማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ለአቶ ሙስጦፌ መሃመድ የክብር ሜዳልያ ሸልሟል፡፡

በእለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የክብር እንግዳውን የሱማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጦፌ መሃመድን፣ የአማራ ክልል ም/ር/መስተዳድር አቶ ላቀ እና ከተለያየ ቦታ ለእለቱ መርሃ ግብር የመጡትን እንግዶች የጣና ፈርጥ ወደሆነችው የባህር ዳር ለተማ እና ወደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በደህና መጣችሁ ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎች ከብዙ ድካም በኋላ ለዚህ ቀን ስለደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
 
ፕሬዚደንቱ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው የመፈለጊያ ጥናት/Tracer Study/ ከተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ ከ80% በላይ የሚሆኑት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ስራ እንደሚየዙ ገልፀው ምሩቃኑም ባበት መስክ ተመራጭ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ተመራቂዎች ብቃት እንደማሳያም ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን የህግ ተመራቂ ተማሪዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ በተሰጠው የመውጫ ፈተና ከፍተኛውን ውጤት ማመዝገባቸውን አስታውሰው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚን ለመቀላቀል ከሚያመለክቱት ውስጥ አመርቂ ውጤት የሚያመጡትም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ይህ ምርቃት ለሁሉም ተመራቂዎች የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን አስታውሰው በቀጣዩ የህይወት ምዕራፋቸው ስኬትን ተመኝተዋል፡፡

 

 
የእለቱ የክብር እንግዳ የሱማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጦፌ መሃመድ ለተመራቂዎች በሱማሌ ብሄራ ክልላዊ መንግስት እና በራሳቸው ስም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታም ሲናገሩ ኢትዮጵያ ከስልጣኔ ማማ ተነስታ አሁን ያለችበት የእሽቁልቁሊት ጉዞ ምክንያቱ በትምህርት/በእውቀት መዳከማችን መሆኑ የማያከራክር እንደሆነ ገልፀው ትምህርት ላይ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የዕውቀት እንጂ የግጭት ቦታ መሆን እንደሌለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻም መልካሙን በመውሰድ፣በማጉልበት ችግሮችን በማስተካከል በመቅረፍ ለሃገራቸው ሰላም እና ብልፅግና እንዲሰሩ ምሩቃኑን አደራ በማለት በቀጣዩ ህይወታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከልብ በመመኘት ንግግራቸውን ቋጭቷል፡፡
 
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በበኩላቸው ተመራቂዎችን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ለሱማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እና ልዑካን በባዕሉ እንዲታደሙ ጥሪ ያቀረቡትን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች አድንቀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በንግግራቸውም ዲግሪ የዕውቀት መጨረሻ ሳይሆን እውቀት ለማግኘት እና ለመመራመር የሚያስችል ስንቅ መሆኑን ጠቁመው ተመራቂዎች ያላቸውን ስንቅ በመጠቀም ለሃገራቸው ብፅግና እንዲሰሩ አደራ ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ባሕር ዳር (የጣና ደሴቶች) የኢትዮጵያውያን የዘር መሰረት የሆነው ኢትዮጵ መገኛ በመሆኗ ታሪካዊ ቦታ እንደሆነ አውስተው ኢትዮጵያውያንን የሚያዛምዳቸው ቋንቋ ሳይሆን ደማቸው በመሆኑ አንድነታቸውን እንዲጠብቁ ተመራቂዎችን አደራ ብለዋል፡፡

 

 
በእለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ የተመረቀ ሲሆን በአራቱ ፕሮግራሞች 6520 የሚሆኑ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 1388 በሁለተኛ ዲግሪ እና 26 ደግሞ በሶስተኛ ዲግሪ ፣37 የሚሆኑት ደግሞ በስቴሻሊቲ ፕሮግራም የተመረቁ ናቸው፡፡ በእለቱ ድምቀት የሰጡት የአማራ ክልል የባህል አምባሳደር የሆነው የሙሉአልም የባህል ማዕከል ባለሙያዎችእና የአማራ ክልል የማርሽ ባንድ እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ ተማሪዎች ሲሆኑ የአፍሪካ የሰርከስ ቡድን አባላትም ልዩ የሆነ ትርኢት አሳይተዋል፡፡