የግዕዝ ጉባኤ

የመጀመሪያው የግዕዝ ጉባኤ ተካሄደ
***********************
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋክልቲ በግዕዝ ቋንቋና ስነ ፅሁፍ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት በፔዳ መሰብሰቢያ አዳራሽ ግንቦት 5/2011 ዓ.ም. ለግማሽ ቀን የግዕዝ ጉባኤና ዐውደ ርዕይ ተካሄደ፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ብቸኛ በሆነባቸው መሬት አስተዳደር እና ማሪታይም አካዳሚ እንደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃችን ከፍ እንዲል የረዳን ቢሆንም የግዕዝ ትምህርት ክፍልን አጠናክረን ብንቀጥል ከዚህ በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን ብለዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ አክልውም በዩኒቨርስቲው የግዕዝ ቋንቋ በትምህርትነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አገራዊ አደራም ጭምር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በጉባኤው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ስለ ግዕዝ ቋንቋና ስነፅሁፍ ህልውና ቁልፍ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ትልቁ ድርሻ ዕውቀትን ማሻገር በመሆኑ ትምህርት ክፍሉ፤ የብዙ ዕውቀቶች ሚስጥር የሆነውን ግዕዝ ማሰልጠን ፣ መሰብሰብ ፣ መተንተን እና ጥናቶችን አጠናቅሮ መያዝ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በበኩላቸው ግዕዝ በዘመናዊ ትምህርት ለምንና እንዴት መሰጠት አለበት በሚለው ሀሳብ መነሻነት ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በፅሁፋቸውም በቋንቋው ዙሪያ እንደ ተግዳሮት ለሚነሱ ጉዳዮች ፡-ግዕዝ የሞተ ቋንቋ ስለሆነ አይሰራበትም፣ በሙያው የሠለጠኑ ምሁራን የሉንም፤ ግእዝን በስርዓተ ትምህርት ለማስገባት በቂ ስዓት የለም በሚሉት ዙሪያ የመፍትሄ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡

በዐውደ ርዕዩም ከፊደል መቁጠር እስከ ቅኔ ሲሰጥበት የነበረበት ሁኔታ፣ የግእዝ ቅኔ ትምህርት የመማር ማስተማሩ ሂደት በተባዕታይ መምህር እና በአንስታይ መሪ እመቤት እንዴት እንደሚሰጥ እና የብራና አዘገጃጀት፣ ከቆዳና ቀለም ዝግጅት እስከ ድጉሳት ድረስ ያለውን ስራ በተግባር ታይቶበታል፡፡