የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ አመታዊ ኮንፈረስ

                       በዘንዘልማ ግቢ አመታዊ ኮንፈረስ እየተካሄደ ነው

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ከአደጋ መከላከል እና ስነምድር ሳይንስ ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር አመታዊ ኮንፈረሱን እያካሄደ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ መክፈቻ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ገድፍ የተገኙ ሲሆን በአገራችን በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች እና የተማረ የሰው ሃይል ቢኖርም በግብርናው ዘርፍ ያለብንን ችግሮች ለመፍታት የሚሰሩ የምርምር ስራዎች በሚፈለገው መጠን ተጨባጭ መፍትሄ እያመጡ አይደለም ብለዋል ፡፡ ስለዚህ በሁለቱ ቀን ቆይታችሁ ባሉን ችግሮቻችን ላይ ትኩረት እንደምታደርጉ ተስፋ አለኝ ብለዋል ፡፡

በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሽመልስ አይናለም የጉባኤው ዋና ጭብጥ  Agriculture and Environmental Management for Sustainable Development”, “Building Disaster Resilient Community”, “Geosciences to Uncover Earth’s Resources መሆኑን ጠቁመው ግብርና የአገሪቱ  ኢኮኖሚ ምሰሶ በመሆኑ የሌሎችን ዘርፎችን ዕድገት እና አጠቃላይ ብሔራዊ ኢኮኖሚያዊ  ዕድገትን ይወስናል ብለዋል::  በተለይም በታዳጊ ሀገራት ድህነትን ለማጥፋት የሚገጥሙትን ዋነኛ ፈተናዎችን ለመሻገር ይህን መሰሉ ጉባኤ ሳይንሳዊ ምርቶች እና የውሳኔ ሃሳቦችን በማመንጨት እረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

መርሀ ግብሩ እስከ ግንቦት 23 የሚቀጥል ሲሆን 29 የሚሆኑት ጥናታዊ ጽሁፎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን ሲቀርቡ ቀሪዎቹ 12 ጥናታዊ ፅሁፎች በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ ጥናቶች  በጥቅሉ  የእንስሳት ምርትና ጤና፣ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ የዓሳና የዱር አራዊት፣ የእርሻ ምርት እና  አስተዳደር ንዑስ ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ ይሆናሉ ፡፡