የውስጥ ግንኙነት

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሚመራ አንድ የልኡካን ቡድን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጎበኘ
------------------------------------------------------------------------------------
 
አርባ አምስት አባላት ያሉትና በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሚመራ አንድ የልኡካን ቡድን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአንድ ቀን ሰፊ ጉብኝት አደረገ፡፡
 
የጉብኝቱ ዋና አካል በሆነውና ልኡካን ቡድኑ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘና ሌሎች የከፍተኛ አመራር አካላት ጋር ባደረገው ውይይት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ከሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን እንደ ባሕር ዳር ካሉ ነባርና የመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች በሶስቱ ዋና ዋና ሂደቶች በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በአመራር፣ በዓለማቀፍ አጋርነትና ሌሎች አበረታች አፈጻጸም በታየባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መውሰድ ስለሚችላቸው ልምዶች ሰፊ ውይይትና የልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡
 
በሌላ በኩል ሁለቱ ተቋማት ወደፊት በተለያዩ ዘርፎች በጋራ መስራት ስለሚችሉባቸው ጉዳዮች በጥልቀት ተወያይተዋል፡፡
 
ልኡካን ቡድኑ ከሰአት በኋላ በነበረው ቆይታ በተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ዋና ዋና ዘርፎች በአካል በመገኘት በቅርቡ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመልካም ምሳሌ የተወሰደበትን የከፍተኛና መካከለኛ አመራር ምርጫ ሂደት ጨምሮ በዋና ዋና ክፍሎች በተጨባጭ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በስፋት ጎብኝቷል፡፡